Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) በአዲስ አበባ የሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ዛሬ ባወጣው አስቸኳይ መግለጫ በሶማሌ ክልል ዶሎ ዞን ሊኖር ስለሚችል የጸጥታ ስጋት አሜሪካውያንን ጨምሮ የውጭ ዜጎች ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳሰበ።

ኤምባሲው በመግለጫው እንዳብራራው፣ ወደ ዶሎ ዞን በሚጓዙ የውጭ ዜጎች ላይ የጸጥታ አደጋ ሊያጋጥም እንደሚችል የሚያመላክቱ መረጃዎች ደርሰውታል። ይህንን ተከትሎም ማንኛውም የአሜሪካ መንግስት ሰራተኛ የተለየ የጸጥታ ፈቃድ ካላገኘ በስተቀር ወደ ዶሎ ዞን እንዳይጓዝ ሙሉ በሙሉ እገዳ ተጥሏል። የሀገሪቱ ዜጎችም በተመሳሳይ ወደዚህ አካባቢ ከማቅናት እንዲቆጠቡ ኤምባሲው ጥብቅ ማሳሰቢያ አስተላልፏል።

ከዚሁ ስጋት ጋር በተያያዘ በአካባቢው የሚገኙ ዜጎች ሊወስዷቸው የሚገቡ የጥንቃቄ እርምጃዎችን ኤምባሲው በአጽንኦት ገልጿል። ዜጎች የተጠቀሰውን አካባቢ እንዲርቁ፣ ሁልጊዜም ንቁ ሆነው ዙሪያቸውን እንዲቃኙ እና ከህዝብ ስብስብ ወይም መጨናነቅ ራሳቸውን እንዲያገሉ መክሯል። ከዚህም ባሻገር እያንዳንዱ ዜጋ የግል የደህንነት እቅዱን እንዲከልስ እና አስገዳጅ ሁኔታ ሲፈጠር አካባቢውን በአፋጣኝ ለቆ ለመውጣት የሚያስችል የመጠባበቂያ እቅድ አዘጋጅቶ እንዲጠብቅ ኤምባሲው አሳስቧል።

እንደ ሐምሊን ዩኒቨርሲቲው ስንታየሁ በላይ ገለጻ፣ ይህ የአሜሪካ ኤምባሲ የጸጥታ ማስጠንቀቂያ በሶማሌ ክልል ዶሎ ዞን እና በአጎራባች የድንበር አካባቢዎች አዲስ የጸጥታ ስጋት እያንዣበበ መሆኑን አመላካች ነው። ኤምባሲው ማስጠንቀቂያውን ሲሰጥ "በውጭ ዜጎች ላይ" ሊቃጣ የሚችል ስጋት መሆኑን ለይቶ መጥቀሱ፣ በአካባቢው ዒላማ ያደረገ የጠለፋ፣ የሽ፣ ብር ወይም የታጠቁ ኃይሎች እንቅስቃሴ ሊኖር እንደሚችል ይጠቁማል።

አክሎም "የአሜሪካ መንግስት ሰራተኞች እና ዜጎች ከዶሎ ዞን እንዲርቁ መደረጉ የችግሩን አሳሳቢነት የሚያሳይ ሲሆን፣ ይህ ሁኔታ በድንበር አካባቢ ባለው የንግድ እና የሰብዓዊ እርዳታ እንቅስቃሴ ላይ የራሱን አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። በቀጣይ የፌደራል መንግስትም ሆነ የክልሉ የጸጥታ ኃይሎች ስለዚህ ጉዳይ የሚሰጡት ማብራሪያ በቀጠናው ያለውን ትክክለኛ የጸጥታ ሁኔታ ይበልጥ ግልጽ ያደርገዋል።" ብሏል።

23 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.