Logo
YenetaTube
የበካይ ጋዝ ልቀት ፍተሻ ከተደረገላቸው 410 የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች መካከል 47% ያህሉ ከደረጃ በታች መሆናቸው ተገለጸ

👉 የተሽከርካሪዎች በካይ ጋዝ ልቀት መጠን ልኬት ከቦሎ ምርመራ ጋር ይካሄዳል ተብሏል።

በአዲስ አበባ ከተማ ድንገተኛ የበካይ ጋዝ ልቀት ፍተሻ ከተደረገላቸው 410 የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች መካከል 47% የሚሆኑት የተቀመጠውን ደረጃ አለማሟላታቸውን የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ለአሐዱ አስታውቋል።

የቢሮው የሞተር አልባ ትራንስፖርት ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ ግርማ ሳሙኤል ለአሐዱ ሬድዮ እንደተናገሩት፣ ድንገተኛ ፍተሻው በአጠቃላይ 787 የሕዝብና የአየር መንገድ ተሽከርካሪዎች ላይ ተካሂዷል።

ከተለኩት የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች መካከል የበካይ ጋዝ ልቀት አነስትኛ መስፈርትን አሟልተው ያለፉት 53% ያህሉ ብቻ እንደሆኑ ገልጸዋል።

የበካይ ጋዝ ልኬቱ በተሽከርካሪዎች ጭስ መውጫ በኩል በቀጥታ እና ከከባቢ አየር ላይ የሚደረግ እንደሆነ አቶ ግርማ አብራርተዋል።

በጭስ መውጫ በኩል የሚደረገው ፍተሻ እንደ ተሽከርካሪዎቹ ሞዴል ዓይነት ታሳቢ ተደርጎ በተቀመጠው ደረጃ መሠረት ይከናወናል ተብሏል።

በመመሪያው መሠረት በፍተሻው የወደቀ ወይም ከደረጃ በታች የሆነ ተሽከርካሪ በ15 ቀን ውስጥ እንዲያስተካክል መመሪያ እንደሚተላለፍለት ተጠቅሷል።

በተሰጠው ጊዜ ካላስተካከለ የ15 ቀን እግድ የሚጣልበት ሲሆን፣ አሁንም ካላስተካከለ እስከ ሦስት ወር ይታገዳል። በዚህ ጊዜ ውስጥ አስተካክሎ ካልቀረበ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ወደ መንገድ እንዳይወጣ ይከለከላል።

በሌላ በኩል የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የአየር ንብረት ለውጥ እና አማራጭ ኢነርጂ ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር አቶ ሰይድ አብደላ፣ ተሽከርካሪዎች ዓመታዊ የቦሎ ዕድሳት ሲያደርጉ የጭስ መጠን ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም የቴክኒክ ደኅንነት ብቻ ይመረመር እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሰይድ፣ አሁን የበካይ ጭስ መጠኑ ተለክቶ ከደረጃ በታች ከሆነ ቦሎ እንደማይሰጥ አስገንዝበዋል።

ተሽከርካሪዎች የበካይ ጭስ መጠናቸውን በጥገና አስተካክለው ቦሎ ከተሰጣቸው በኋላም የክትትል ሥራው እንደሚቀጥል አብራርተዋል።
#አሐዱ

26 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.