Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) የሰው ልጅን ህልውና ሊያጠፋ ይችላል በሚል የቴክኖሎጂው ዘርፍ መሪዎች የሚያቀርቡትን ሥጋት "በአክራሪ ዴሞክራቶች የሚራገብ የፈጠራ ወሬ" ሲሉ አጣጥለውታል። ትራምፕ ይህንን ያሉት፣ በዘርፉ ግዙፍ ከሚባሉት ተቋማት የተሰማውን ከባድ ማስጠንቀቂያ ውድቅ ባደረጉበት ወቅት ነው።

የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የደህንነት ጉዳይ ዳግም አነጋጋሪ የሆነው ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ የ'አንትሮፒክ' ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዳሪዮ አሞዴይ የቴክኖሎጂውን አደጋ ለመገምገም ጊዜ እንዲሰጥ እና ልማቱ እንዲገታ የሚጠይቅ ጽሑፍ ማውጣታቸውን ተከትሎ ነው። ይህንን ጥሪ የቻት ጂፒቲ ፈጣሪ የሆነው የ'ኦፕን ኤአይ' ኃላፊ ሳም አልትማን እና የ'ግሮክ' ቻትቦት ባለቤት የሆነው ኢሎን ማስክ ጭምር ደግፈውታል። ዳሪዮ በጽሑፋቸው ላይ ቴክኖሎጂው ራሱን በራሱ የማሳደግ አቅሙ በመጨመሩ ከክረምቱ ጀምሮ "በአስደንጋጭ ፍጥነት" እያደገ መሆኑን እና በቅርቡም የኦፕን ኤአይ ሲስተሞች ያለምንም ትዕዛዝ የውጭ መረቦችን ሰብረው መግባታቸውን እንደ ከባድ ማሳያ ጠቅሰዋል።

ይሁንና ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሰኞ ዕለት በ'ትሩዝ ሶሻል' ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ተከታታይ መልዕክት፣ ይህ ሥጋት "ተስፋ በማይቆርጡ ነገር ግን ብዙም በማያሸንፉ የግራ ዘመም ዴሞክራቶች" የሚሰራጭ የፖለቲካ ሴራ ነው ብለዋል። ከቻይና ጋር ያለውን የቴክኖሎጂ ፉክክር ያስታወሱት ትራምፕ፣ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን እና የዳታ ማዕከላትን "በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የኢኮኖሚ ልማት ሞተር" ሲሉ አወድሰዋቸዋል።

አክለውም "እኔ የፈጠራ ወሬዎችን አክሻፊ ነኝ፤ ኤአይ (AI) ዓለምን ያጠፋል፣ ሮቦቶችም ከተሞቻችንን ይወርራሉ የሚባለው፣ የአየር ንብረት ለውጥ ዓለምን ያጠፋታል እንደተባለው ዓይነት የውሸት ትርክት ነው" ሲሉ ቴክኖሎጂው በዘመናቸው እንደማይገታ አጽንኦት ሰጥተዋል። ይህንን የኤአይ (AI) ሥጋትም እ.ኤ.አ. በ2016ቱ ምርጫ ላይ ሩሲያ ጣልቃ ገብታለች ከተባለበት የፖለቲካ ውንጀላ ጋር አነጻጽረውታል።

የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ደህንነት ጉዳይ ከሳይንሳዊ ሥጋትነት አልፎ የፖለቲካ እና የጂኦ-ፖለቲካ ፉክክር ማዕከል እየሆነ መምጣቱን እንገነዘባለን። ቴክኖሎጂውን የፈጠሩት ጠበብት "ከቁጥጥር ውጭ እየሆነብን ስለሆነ ረጋ እንበል" ሲሉ ፖለቲከኞች ደግሞ "ከቻይና ወደኋላ መቅረት የለብንም፤ የኢኮኖሚያችን ሞተር ነው" በማለት የባለሙያዎቹን ሥጋት በፖለቲካ መነጽር እያጣጣሉት ይገኛሉ። የደህንነት ጥንቃቄን ወደ ጎን በመተው ለኢኮኖሚ እና ለዓለም አቀፍ የበላይነት ሲባል ብቻ ቴክኖሎጂውን ያለገደብ መልቀቅ፣ አሜሪካን ብቻ ሳይሆን መላውን የዓለም ሕዝብ ላልተጠበቀ አደጋ ሊያጋልጥ የሚችል ከባድ የታሪክ አጋጣሚ ላይ መሆናችንን ያሳያል።

እናንተስ በማንኛው ሀሳብ ትስማማላችሁ?

26 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.