Logo
EBC
ታሪካችንን በራሳችን ብዕር፡ የኢትዮጵያ የድልና የተስፋ አዲስ ዓመት
(የዕለቱ መልዕክት)
*******************

የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ተፈጥሮ ራሷን የምታድስበት፣ የደፈረሱ ወንዞች የሚጠሩበት፣ ምድሪቱ በአደይ አበባ የምታጌጥበትና የመስቀል ወፎች ብቅ የሚሉበት ልዩ ወቅት ነው።

ይህ የተፈጥሮ ዑደት ለሀገራችን የብሩህ ተስፋና የአዲስ ምዕራፍ መጀመሪያ ተደርጎ ይወሰዳል።

አዲሱ ዓመት ከምንጊዜውም በተለየ ሁኔታ ፈተናችንን ከኋላ ትተን፣ ተስፋችንን ከፊት በማስቀደም ፊታችንን ወደ ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግና የምናዞርበት ታሪካዊ አጋጣሚ ነው።

እየተከናወኑ ያሉ ሰፋፊ የልማት ሥራዎች በተለይም የኮሪደር ልማቱን ጨምሮ የተጀመሩ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ሀገራዊ ራዕይን እውን የማድረግ ማሳያዎች ናቸው።

"የምንሠራው ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለነገ እና ለቀጣዩ ትውልድ ነው በሚል መርህ፣ ለትውልድ የሚሻገር ዘላቂ ሥራ እየተሠራ ይገኛል።

ኢትዮጵያ ብልጽግናዋንና ድሎቿን ለመጻፍ ስትነሳ መጻፊያ ብዕሯ ዜጎቿ ሲሆኑ፣ ቀለሙም ከእያንዳንዱ የላብና የትጋት ውጤት የሚቀዳ ነው።

ኢትዮጵያ ፈተናን ወደ ዕድል በመቀየር ታሪክ ከሚያነሣቸው ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ የሚያስችል በቂ አቅምም ሆነ ጽኑ አቋም አላት፤ ለዘመናት ያቆየችው የነጻነት ታሪክም የዚሁ ማሳያ ነው።

አዲሱ ዓመት ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን ይበልጥ የሚጸናበትና ዴሞክራሲያዊ ዕሴቶቻችን ሥር ሰደው የሚጎለብቱበት እንዲሆን እያንዳንዳችን የድርሻችንን መወጣት ይጠበቅብናል።

በሀገር ፍቅር የታነጸ፣ አካባቢያዊ ማንነቱን ከሀገራዊ ማንነቱ ጋር አዋሕዶ የያዘ፣ ለፈጠራ የተጋለጠና ያልተሄደበትን መንገድ ለመጓዝ ድፍረት ያለው ትውልድ መፍጠር የዘመኑ ግዴታ ነው።

አዲስ ዓመት አዲስ ተስፋን ይዞ የሚመጣው፣ እኛ ራሳችንን ለለውጥ ባዘጋጀንበት ልክ ብቻ ነው።

በሀገር ጉዳይ ላይ ጣት ከመጠቆም ይልቅ፣ “ከእኔ ምን ይጠበቃል?” የሚለውን ጥያቄ በማስቀደም ለጋራ ራዕይ መትጋት ይኖርብናል።

የሚጎዱንን አሮጌ አስተሳሰቦች ወደ ጎን ትተን፣ ጠቃሚ በሆኑ አዳዲስ ዕሴቶች መተካት የመጻኢው ጉዟችን መሠረት ነው።

ጊዜው ለሁሉም ባዶ ሆኖ የቀረበ አዲስ የዘመን መጽሐፍ ገልጦልናል። የዚህ መጽሐፍ ዋና ጸሐፊዎች እኛው ራሳችን ነን። እኛ ዝም ብንል ሌሎች በፈለጉት መንገድ ሊጽፉት እንደሚችሉ መገንዘብ ያሻል።

ይሁንና የራሳችንን የዘመን አቆጣጠር የፈጠርን ሕዝቦች፣ የራሳችንን ዕጣ ፈንታ በገዛ እጃችን ከመጻፍ የሚያግደን ምንም ዓይነት ኃይል የለም።

እኛው አቅደን፣ እኛው ሠርተን፣ ችግሮቻችንን በውይይትና በምክክር ፈትተን የራሳችንን ጉዳይ በራሳችን የመወሰን ባህል መለማመድ ጀምረናል፤ አቅሙም እንዳለን አሳይተናል።

ዘመኑ የኢትዮጵያውያንና የአዲሲቱ ኢትዮጵያ ነው። ዜጎች ልዩነታቸውን ጠብቀው በጋራ ጉዳዮች ላይ በአንድነት ሲቆሙና እርስ በርስ ሲደጋገፉ፣ የሀገራችን የብልጽግና ብዕር የላቀ አሸናፊነትን፣ ታላቅነትንና አንጸባራቂ ድልን አድምቆ ይጽፋል።

የኢቢሲ ዶትስትሪም ኤዲቶሪያል

29 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.