Logo
FBC
የድሮን ቴክኖሎጂ ለኢትዮጵያ ሁለገብ ዕድገት

አዲስ አበባ፣ መስከረም 1፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) አዲሱን ዓመት ለመቀበል በአዲስ አበባ ሰማይ ላይ የተካሄደው አስደናቂ የድሮን ትርኢት፣ ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው ዘርፍ እያሳየች ያለችውን ፈጣን ዕድገትና የምጥቀት ደረጃ በግልጽ ያበሰረ ታሪካዊ አጋጣሚ ሆኗል።

3 ሺህ ድሮኖች በአንድነት ተቀናጅተው የአዲሱን ዓመት ዋዜማ በልዩ ድምቀት ሲያበሩ የከተማዋ ሰማይ የጥበብ፣ የፈጠራና የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ውህደት መድረክ ሆኖ አምሽቷል።

ይህ ትርዒት ለሕዝቡ የቀረበ የብርሃንና የቀለማት ውበት ብቻ ሳይሆን ሀገራችን በዘመናዊ የድሮን ቴክኖሎጂና በዲጂታል ዘርፍ የምታደርገውን ታላቅ ጉዞ የሚያሳይ አዎንታዊ ማረጋገጫ ነው።

በአሁኑ ወቅት የድሮን ቴክኖሎጂ ለመዝናኛና ለሕዝባዊ በዓላት ትርኢት ብቻ ሳይሆን ዘርፈ ብዙ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

በዚህ የዲጂታላይዜሽን ጉዞ ውስጥ ደግሞ እየተከናወኑ የሚገኙ አበረታች ጥረቶች ሀገሪቱን በቴክኖሎጂው ዘርፍ በምሥራቅ አፍሪካ ግንባር ቀደም የማድረግ ዓላማ ያላቸው ናቸው።

በአዲሱ ዓመት ዋዜማ የታየው በርካታ ድሮኖችን በላቀ ስልተ ቀመር አቀናጅቶ የመምራት አቅም ኢትዮጵያ በዘመናዊ ሶፍትዌር፣ በሳይበር ደኅንነትና በኤሮኖቲክስ ኢንጂነሪንግ ዘርፍ እያደገ የመጣ የሰው ኃይልና መሠረተ ልማት እንዳላት በግልጽ ያሳያል።

በተጨማሪም የድሮን ቴክኖሎጂን በሀገር ውስጥ የመገጣጠም፣ የጥገናና የሶፍትዌር ሥርዓቶችን የመቅረጽ አቅም ማደጉ ኢትዮጵያ አቪዬሽን መስክ የምታደርገውን ጉዞ ያፋጥነዋል።

እንዲሁም በግብርና፣ በጤና፣ በከተሞች ልማትና በመሠረተ ልማት ግንባታ ሂደቶች ውስጥ የድሮን አጠቃቀም እየሰፋ መምጣቱ ለሀገሪቱ ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ለማበርከት የሚያስችል ነው።

ከዚህ ባሻገር እየተጠናከረ የሚገኘው የቴክኖሎጂ ሽግግር እና በሀገር ውስጥ የበለጸጉ ሥርዓቶችን የመጠቀም ልምድ የውጭ ጥገኝነትን ለመቀነስ ያስችላል።

በአጠቃላይ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ የአዲስ አበባን ሰማይ ያሸበረቀው የድሮን ትርኢት ለወጣቶች፣ ለተመራማሪዎችና ለፈጠራ ባለቤቶች ትልቅ ተስፋና መነቃቃትን የፈጠረ ነው።

የሀገራችንን ባህል፣ የታሪክ ቅርሶችና የዲጂታል ኢትዮጵያ ራዕይን በሰማይ ላይ በሥዕላዊ መንገድ ማሳየቱ ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ራስን ለመቻል በምታደርገው ጉዞ ትክክለኛ መንገድ ላይ መሆኗን ያመላክታል።

በአብረሃም አበራ

29 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.