Logo
FBC
ከብዛት ወደ ምርታማነት የተሸጋገረው የእንስሳት ሃብት

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በእንስሳት ሃብት ብዛት በአፍሪካ ቀዳሚ ከሆኑ ሀገራት መካከል ትጠቀሳለች፡፡

በዘርፉ ያለውን እምቅ አቅም በሚገባ በመጠቀም ለኢኮኖሚ እድገትና ለማህበረሰብ ጥቅም ከማዋል አንጻር ውስንነቶች ነበሩ፡፡

የዝርያ ጥራት፣ የመኖ አቅርቦት፣ የእንስሳት ጤና፣ ቴክኖሎጂና የገበያ ትስስር ውስንነትም የዘርፉን ምርታማነት ከገደቡ ዋና ችግሮች መካከል ናቸው፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት ግን ትኩረቱ ከእንስሳት ቁጥር ጭማሪ ባለፈ፣ ከዘርፉ የሚገኘውን ምርት ማሳደግ፣ የአርቢዎችን ገቢ ማሻሻልና የእንስሳት ተዋጽኦን ወደ ውጭ ገበያ ማስፋት ላይ ሆኗል።

የዚህ ለውጥ አንዱ መገለጫም የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ሲሆን ÷ የወተት፣ የዶሮና እንቁላል፣ የማርና የዓሣ ልማትን በተቀናጀ መልኩ ማሳደግ ላይ ትኩረት አድርጓል።

በወተት ልማት የተሻሻሉ ዝርያዎች፣ ሰው ሰራሽ ማዳቀል፣ የመኖ አቅርቦትና የእንስሳት ጤና ላይ በተሰራው ሥራ በመነሻ ዓመቱ ወደ 500 ሺህ ገደማ የነበረው የማዳቀል አገልግሎት በ2018 ዓ.ም. ወደ 3 ነጥብ 8 ሚሊየን አድጓል።

የወተት ምርትም ከ7 ነጥብ 1 ቢሊየን ሊትር ወደ 15 ነጥብ 2 ቢሊየን ሊትር ማደጉን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

በዶሮና እንቁላል ልማትም የአንድ ቀን ጫጩት አቅርቦት ከ26 ሚሊየን ወደ 136 ሚሊየን፤ የእንቁላል ምርት ከ3 ነጥብ 2 ቢሊየን ወደ 9 ነጥብ 3 ቢሊየን ከፍ ብሏል።

ይህም የዶሮ እርባታን ከቤተሰብ ፍጆታ ባሻገር ወደ ገቢ ማመንጫና የንግድ ሥራ ለማሸጋገር ያለውን አቅም ያሳያል።

ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት ምርትን በመጨመር ብቻ አልተወሰነም፤ ከአርቢው እስከ ገበያ ያለውን የእሴት ሰንሰለት ለማጠናከርም ሥራዎች ተከናውነዋል።

በወተት፣ ሥጋ፣ ዶሮና እንቁላል እንዲሁም ዓሣ ልማት ላይ የአምራቾችን ምርታማነትና የንግድ አቅም ለማሳደግ የተደረጉ ጥረቶችን ለማገዝ የዓለም ባንክ 176 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ያደረገለት የእንስሳትና ዓሣ ሃብት ዘርፍ ልማት ፕሮጀክትም ተግባራዊ ሆኗል።

በተጨማሪም የእንስሳት ኤክስቴንሽንና የጤና ሥርዓቶች ተጠናክረዋል። በ2018 ዓ.ም. የብሔራዊ የእንስሳት ጤና መረጃ ሥርዓት ለመገንባት የተጀመረው ሥራ ዘርፉን በዲጂታል መረጃ ለመምራት የተወሰደ ርምጃ ነው፡፡

በሌላ በኩል የንብ ሃብት መረጃ አስተዳደር ሥርዓትም በመረጃ የተደገፈ የማር ልማትን ለማስፋት አዲስ አቅጣጫ ከፍቷል።

በአጠቃላይ ከ2010 ዓ.ም. ወዲህ የተከናወኑት ሥራዎች ዋና አቅጣጫቸውን ከ“እንስሳት ብዛት” ወደ “እንስሳት ምርታማነት” ማሸጋገር ላይ ትኩረት አድርገዋል።

የተሻሻለ ዝርያ፣ መኖ፣ የእንስሳት ጤና፣ ዘመናዊ እርባታ፣ ኤክስቴንሽን፣ የገበያ ትስስርና ዲጂታል መረጃ በአንድ ላይ መገናኘታቸውም ዘርፉን ወደ ምርታማና ተወዳዳሪ የኢኮኖሚ ዘርፍ ለመቀየር መሠረት ጥሏል።

በአመለወርቅ ደምሰው

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.