Logo
SeledaPost
ኦባሳንጆ በሕወሓት መሪዎች ለቀረበባቸው የገለልተኝነት ቅሬታ ምላሽ ሰጡ

የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት አሸማጋይ የነበሩትና የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ፣ በሕወሓት መሪዎች ለቀረበባቸው የገለልተኝነት ቅሬታ ምላሽ ሰጡ።

ኦባሳንጆ በጽሕፈት ቤታቸው በኩል ባወጡት መግለጫ፣ በሁለቱ ወገኖች መካከል ውጥረት መባባሱንና የፕሪቶሪያ ስምምነቱን የሚጥሱ እንቅስቃሴዎች መታየታቸውን ተከትሎ የማሸማገል ጥረት መጀመራቸውን ገልጸዋል።

አሸማጋዩ እስካሁን ያከናወኑት ሥራ በተሳካ ሁኔታ ሲካሄድ እንደቆየ ጠቅሰው፣ በማሸማገል ሂደቱ ከኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት ትዕዛዝ እንደማይቀበሉ አስታውቀዋል።

በተጨማሪም ምሥጢራዊ የድርድር መረጃዎችን ለሕዝብ ይፋ ማድረግ ኃላፊነት የጎደለው አሠራር ነው ብለዋል።

ኦባሳንጆ፣ አንዳንድ የሕወሓት አመራሮች የማሸማገል ጥረታቸውን ለማጣጣል መሞከራቸው አዲስ እንዳልሆነ ገልጸው፣ በፕሪቶሪያ ድርድር ወቅትም ተመሳሳይ ሙከራ መደረጉን ጠቁመዋል።

አንድን ወገን ያዳላሉ የሚለው ክስ የአደራዳሪነት ሥራቸውንና የተሰጣቸውን ውክልና የሚያዛባ መሆኑን የገለጹት ኦባሳንጆ፣ በድርድር ሂደት የአንድ ወገንን ፍላጎት በሌላው ላይ በኃይል መጫን ውጤታማ መፍትሔ እንደማያመጣ አስምረውበታል።

የሕወሓት መሪዎች በበኩላቸው ባለፈው እሁድ ባወጡት መግለጫ፣ ኦባሳንጆ በማሸማገል ሂደቱ የገለልተኛ አደራዳሪነት መርኅን አልጠበቁም ሲሉ መውቀሳቸው ይታወሳል።

Seledadotio
Seledadotio
1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.