Logo
EBC
የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን፡ ቃልን በተግባር ያረጋገጠ ጉዞ
*******************
(የዕለቱ መልዕክት)

ኢትዮጵያችን ዛሬ ታሪካዊ በሆነ የማንሰራራት ምዕራፍ ላይ ትገኛለች።ዛሬ ጳጉሜ 2 "የማንሰራራት ቀን" ተብሎ ሲከበር ይህ ጽንሰ-ሀሳብ ዝም ብሎ ምኞት ሳይሆን በተጨባጭ መሬት ላይ እየታዩ ያሉ ስኬቶች ማሳያ ነው።

ባለፉት የለዉጥ ዓመታት የነበሩት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የተቋማት ግንባታ እና ሌሎች ሪፎርሞችን የማድረግ ስራዎች ተጠናቀው አሁን የዘላቂ ልማት ትሩፋቶችን ለቀጣዩ ትውልድ የማሸጋገር ጊዜ ላይ ደርሰናል።

በትናንት ለቅሶና እሳቤ ታጥረው ከሚኖሩት ይልቅ ብሩህ የወደፊት ተስፋን ሰንቀው ወደ ሚቀጥለው አዲስ ምዕራፍ የሚሸጋገሩ ዜጎች ለዚህ ሀገራዊ ማንሰራራት ዋነኛ ሞተር ናቸው።

ይህ ሀገራዊ ማንሰራራት በግብርናው ዘርፍ፣ በማዕድንና በቡና ወጪ ንግድ እንዲሁም በተኪ ምርት ታሪክ ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቧል። በተለይም እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያሉ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ዳር ማድረስ የጀግንነት፣ የወል ትርክት እና የ"ይቻላል" መንፈስ ህያው ምስክር ሆኗል።

መንግስት ወደ ተግባር ያስገባው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ፣ የአገልግሎት ዘርፍ ልህቀትን በማረጋገጥ እና ለአምራች ኢንዱስትሪው የፋይናንስ አቅርቦትን በማሳደግ ጥራት ያለው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንዲረጋገጥ ትልቅ አቅም ፈጥሯል።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከግብርና መርነት ተላቆ ብዝሃ ዘርፎችን ማዕከል ወዳደረገ መዋቅራዊ ስርዓት መሸጋገሩ፣ የሀገራችን የኢኮኖሚ መሰረት ይበልጥ አስተማማኝ እያደረገው ይገኛል።

የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ ይበልጥ ወደ ላቀ ከፍታ የሚያሸጋግሩት በጉባ ይፋ የተደረጉት ግዙፍ አዳዲስ ፕሮጀክቶች መከናወን መጀመራቸው የዘመኑ ታላቅ ብስራት ነው።

እነዚህ ግዙፍ ፕሮጀክቶች፤ ሀገር በቀል የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታን፣ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ፕላንትን፣ አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ግዙፉን የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያን፣ የ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ቤቶች ግንባታን እና የነዳጅና ጋዝ ልማት ያካተቱ ናቸው። ፕሮጀክቶቹ የኢትዮጵያን የወደፊት እጣ ፈንታ ከመወሰንም ባሻገር የሀገራችንን የፕሮጀክት አፈፃፀም ፍጥነት፣ ጥራትና ብቃት በተግባር የሚያስመሰክሩ ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ማንሰራራት ቀጠናዊ እና አለም አቀፋዊ ተፅዕኖዋን በሚመጥን መልኩ እያደገ ነው። ሀገራችን የብሪክስ (BRICS) አባል መሆኗን ተከትሎ አሁን የተጀመሩት እንደ ኒውክሌር ፕላንት እና አቪዬሽን ያሉ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ልማት ፕሮጀክቶች ከውጭ ሀገራት ጋር የምናደርገውን የኢኮኖሚ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ትብብር ይበልጥ ያጠናክሩታል።

ወጣቱ ትውልድ በዲጂታል ኢኮኖሚ፣ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እና በእውቀት ላይ በተመሰረተ የፈጠራ ስራ ላይ መሳተፍ መጀመሩ ይህን ሀገራዊ ማንሰራራት ወደማይቀለበስበት ደረጃ ያደርሰዋል።

የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ማሻሻያው እውነተኛ ትርጉም የሚያገኘውም ይህ የሰው ሃይል ግንባታ ከዘላቂ የሰላም ግንባታ፣ ጠንካራ የጸረ-ሙስና ትግል እና የፍትህ ስርዓት መሻሻል ጋር ተሰናስሎ ሲጓዝ ነው።

ይህ የማንሰራራት እና የማጽናት ጉዞ ዘላቂ እንዲሆን ሁላችንም አሮጌውንና የማይጠቅመውን አስተሳሰብ አውልቀን በመጣል፣ አዲሱን የለውጥና የስራ ባህል መላበስ ይገባናል።

እርስ በእርስ ከመጠላለፍና ጣት ከመቀሳሰር ወጥተን፣ በሌት ተቀን ትጋት፣ በቅንነት፣ እንዲሁም በነቃ ከተሳትፎ፤ ብልጽግናዋ ያረጋገጠች ኢትዮጵያን ለትዉልድ ማቆየት እንችላለን።

አዲሱ ዓመት ሀገራዊ ማንሰራራትን በተግባር የምናረጋግጥበት፣ ጀግንነትንና የወል ትርክትን አጠናክረን የምንቀጥልበት የብሩህ ተስፋ ዘመን ነው!

የኢቢሲ ዶትስትሪም ኤዲቶሪያል

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.