Logo
YenetaTube
የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተክርስቲያን አቶ ጌትነት ለማን ከአገልግሎትና ውክልና አገደች

የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተክርስቲያን ዋና ጽሕፈት ቤት በነሐሴ 29 ቀን 2018 ዓ.ም በጻፈው ይፋዊ ደብዳቤ፣ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ጠቅላይ ፀሐፊ አቶ ጌትነት ለማ ከማንኛውም የቃለ ሕይወት ቤተክርስቲያን አገልግሎትና ውክልና ታግደው እንዲቆዩ መወሰኑን አስታወቀ።

በዋና ጸሐፊው በዶክተር ስምኦን ሙላቱ የተፈረመው ይህ ደብዳቤ እንደሚያስረዳው፣ ውሳኔው የተላለፈው በአቶ ጌትነት ለማ የሕይወትና የአገልግሎት ንጽሕና ላይ በማህበራዊ ሚዲያና በምዕመናን ዘንድ የተሰራጩ አሉታዊ ዘገባዎችን አስመልክቶ ቤተክርስቲያኗ ማጣራት በማድረጓ ነው።

ቀደም ሲል የቤተክርስቲያኗ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በነሐሴ 22 ቀን 2018 ዓ.ም ከአቶ ጌትነት ጋር ውይይት አድርጎ እንደነበርና የተነሱት ክሶች እውነት ከሆኑ ንስሐ እንዲገቡ፣ ካልሆኑ ደግሞ ቤተክርስቲያኗ እውነቱን በማጣራት አስፈላጊውን እርምጃ እንደምትወስድ ማሳወቋ ተገልጿል።

በዚህም መሠረት የቤተክርስቲያኗ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በነሐሴ 28 ቀን 2018 ዓ.ም ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ በመተዳደሪያ ደንቡ አንቀጽ 158.2 መሠረት የቀረቡት ክሶች በቦርድ ተጣርተው ውሳኔ እስከሚያገኙ ድረስ፣ ከነሐሴ 29 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ አቶ ጌትነት ለማ ከማንኛውም የቃለ ሕይወት ቤተክርስቲያን አገልግሎትና ውክልና ታግደው እንዲቆዩ ወስኗል።

በተጨማሪም ቤተክርስቲያኗ በዚህ ጊዜ ውስጥ ለአቶ ጌትነት ለማና ለቤተሰባቸው እግዚአብሔር በረዳቸው መጠን በፊቱ በንስሐ፣ በጸሎትና በምክር እንዲያልፉ እድል ለመስጠት የታሰበ መሆኑን ገልጻለች።

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.