Logo
SeledaPost
የደቡብ ኮሪያ ጠንቋዮች AI ገቢያችንን ክፋኛ ቀንሶብናል ብለው አማረሩ

በቴክኖሎጂ ምጥቀት ቀዳሚ ከሆኑት የዓለማችን አገራት መካከል አንዷ በሆነችው ደቡብ ኮሪያ፣ የቅርብ ጊዜው የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ዕድገት የዘመናት ታሪክ ባለው የባህላዊ ዕድል ትንበያ (ጥንቆላ) ኢንደስትሪ ላይ ከፍተኛ አደጋ እየደቀነ መሆኑ ተሰማ።

በአገሪቱ የሚገኙ ታዋቂ ዕድል ተንባዮችና ጠንቋዮች ወደ እነርሱ ይመጡ የነበሩ ደንበኞቻቸው ፊታቸውን ወደ AI ቴክኖሎጂ በማዞራቸው ምክንያት ሥራቸው ክፉኛ እንደ ተቀዛቀዘባቸው በምሬት በመግለጽ ላይ ናቸው።

በዋና ከተማዋ ሴኡል ዳርቻ በሚገኘውና በባህላዊ ዕድል ተንባዮች (ጠንቋዮች) መንደርነቱ በሚታወቀው ‘ሚያ መንደር’ ውስጥ አሁን ላይ የደንበኞች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል።

ቀደም ባሉ ዓመታት የደቡብ ኮሪያ ነዋሪዎች ስለ ጤናቸው፣ ትዳር፣ ፍቅር፣ ገንዘብ እና የወደፊት ዕጣ ፈንታቸው ለመጠየቅ ወደዚህ መንደር በብዛት ይጎርፉ ነበር። ይሁን እንጂ ዛሬ ላይ አብዛኞቹ ዜጎች በአካል ወደ መንደሩ ከመሄድ ይልቅ በኢንተርኔት አማካኝነት እንደ ChatGPT እና Gemini ያሉ የ-AI መተግበሪያዎችን በመጠቀም ዕድላቸውን መተንበይ መምረጣቸው ተገልጿል።

በዚሁ መንደር ውስጥ ከቀሩት ጥቂት ዕድል ተንባዮች መካከል አንዷ የሆኑት የ86 ዓመቷ አዛውንት ሶንግ ኦ-ሱን ሁኔታውን ሲያስረዱ፣ እሳቸው አሁንም ከዘመናዊው የኢንተርኔት ዓለም ርቀው እንደሚኖሩና ዕድልን ለመተንበይ “አራቱ የዕጣ ፈንታ ምሰሶዎች” (Saju) የሚባለውን የኮሪያ ጥንታዊ ኮከብ ቆጠራ ዘዴ በብሬይል መጽሐፍ እያነበቡ እንደሚጠነቁሉ ገልጸዋል።

አዛውንቷ ባለፉት 40 ዓመታት ያካበቱት ይህ የሰዎች ስነ-ልቦና የመረዳትና የማማከር ልምድ AI በቀላሉ ሊተካው የማይችለው የላቀ ሰብአዊ ችሎታ መሆኑን በጽኑ ያምናሉ። “በሕይወት የመኖር ተስፋ ቆርጠው ለመሞት እንኳ ወደ እኔ የመጡ ሰዎችን አሳምኜና አጽናንቼ ሕይወታቸውን እንዲቀጥሉ አድርጌያለሁ” ሲሉም የሥራቸውን ማኅበራዊ ፋይዳ ያስረዳሉ።

Seledadotio
Seledadotio
1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.