Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) በደቡብ ሱዳን የተገደሉት 2 የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች የሽኝትና የሀዘን መግለጫ ስነስርአት ተከናወነ፡፡ በዛሬው እለት በደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ ጁባ የሀዘን መግለጫ ስነስርአትና የአስከሬን ሽኝት ፕሮግራም መከናወኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዘግቧል፡፡ እንደዘገባው ይህ ፕሮግራም የተካሄደው ከቀናት በፊት በጆንግሌይ ግዛት በተከፈተ ተኩስ ህይወታቸው ላለፈው የኢትዮጵያ ወታደሮች ነው፡፡ እነዚህ ወታደሮች የተመድ የደቡብ ሱዳን ተልእኮ አባላት መሆናቸውን ጠቅሶ በልኡኩ ተሸከርካሪ ላይ በተፈፀመ ጥቃት ህይወታቸው ማለፉን ‹‹ለሰላም የተከፈለ መስዋእትነት ነው›› ብሎታል፡፡

የልኡኩ ሀላፊና የተመድ ዋና ፀሀፊ ተወካይ አኒታ ኪኪ አጎቦ በስፍራው ተገኝተው ባሰሙት ንግግር የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሀይሎች ለደቡብ ሱዳን ህዝብ ላሳዩት ቁርጠኝነት ምስጋናቸውን አቅርበው እ.ኤ.አ ከ2014 አንስቶ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ በማያወላውል ሙያዊ ብቃትና ጀግንነት ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልፀዋል፡፡ ጨምረውም ‹‹እነዚህ ህይወታቸው ያለፈ ሰላም አስከባሪዎች ወደዘላለም ቤታቸው የሄዱ ቢሆንም ውርሳቸውና ተፅእኗቸው ጥሩ መታሰቢያ ይሆናል፡፡ ሰላም ማስከበር ሙያ ብቻ ሳይሆን እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ማገዝም ጭምር ነው፡፡ ህይወታቸውን የከፈሉበትን አላማ እናከብራለን›› ብለዋል፡፡ በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ ጉዳይ አስፈፃሚው አክሊሉ ታደሰ በበኩላቸው ‹‹እነዚህ በድፍረትና በቁርጠኝነት ሲቪሎችን ለመጠበቅ ተሰልፈው ለሌሎች ሲሉ ህይወታቸውን ያጡ ጀግኖች ናቸው፡፡ ዛሬ በአስከሬናቸው አበባ ስናስቀምጥ አገልግሎታቸውንና የተሰለፉለትን አላማ እያከበርን ነው፡፡ መስዋእትነታቸው ፈፅሞ አይረሳም›› ብለዋል፡፡

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.