Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) በነዳጅ በበለፀገችው ኢራን መኪናዎች ነዳጅ ለመቅዳት ረጅም ሰልፍ መጠበቅ ጀምረዋል፡፡ በያዝነው ሳምንት በቴሄራንና ሌሎችን ቁልፍ የኢራን ከተሞች በነዳጅ ማደያዎች ላይ ረጅም የተሸከርካሪዎች ሰልፍ እንደሚታይ ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡ እንደዘገባው በኢራን ውስጥ ያጋጠመው የነዳጅ እጥረት በርካታ ማደያዎች እንዲዘጉ ወይንም አቅርቦታቸውን እንዲገድቡ ያስገደደ ሆኗል፡፡

አሽከርካሪዎች ወደተለያዩ ነዳጅ ማደያዎች በመሄድ ፍለጋ ቢያደርጉም አብዛኛዎቹ ዝግ ሆነው እንዳገኟቸው የገለፁ ሲሆን ነዳጅ ባለባቸው ማደያዎች ደግሞ ከሁለት ወይንም ከዚያ በላይ ሰአታትን ተሰልፈው ለመጠበቅ መገደዳቸውን ለዜና አውታሩ ተናግረዋል፡፡ የኢራን ሚዲያዎችን በምንጭነት የጠቀሰው ዘገባው በምስራቅና ደቡባዊ ቴሄራን የሚገኙ ነዳጅ ማደያዎች ከሞላ ጎደል ዝግ የሆኑ ከመሆኑም በላይ እንደካራጅና ማሻድ ያሉ በአቅራቢያው የሚገኙ ትልልቅ ከተሞች ውስጥም ማደያዎቹ ለጊዜው ተዘግተዋል፡፡ እንደዘገባው አንዳንድ ማደያዎች አንድ መኪና 20 ሊትር ብቻ እንዲቀዳ የሚል ገደብ ጥለዋል፡፡

በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በኢራን ከተሞች ያለውን የነዳጅ ሰልፍ የሚያሳዩ ቪዲዮዎች በስፋት በመሰራጨት ላይ ናቸው፡፡ የኢራን ኢነርጂ ኦፕቲሚሽን ድርጅት እንደገለፀው አገሪቱ በየቀኑ የነዳጅ ፍላጎቷ ወደ135 ሚሊዮን ሊትር መሆኑን ጠቅሶ ከከዚህ ውስጥ ከ14 እስከ 15 ሚሊዮን ሊትር የሚጠጋ እጥረት እያጋጠማት ነው፡፡ የኢራን ባለስልጣናት በጦርነቱ የነዳጅ ማጣሪያዎችና ማከማቻዎች ላይ የደረሰው ጉዳት ይህንን እጥረት እንደፈጠረው በመናገር ላይ ናቸው፡፡ ከውጭ ነዳጅ ለማስገባትም የተጣለው ማእቀብ እንቅፋት እንደፈጠረባቸው አስረድተዋል፡፡ በአለም ላይ ከፍተኛ የድፍድፍ ነዳጅ ክምችት ካላቸው አገራት አንዷ የሆነችው ኢራን በማጣሪያዎቿ ላይ የደረሰው ጉዳት የአገር ውስጥ የነዳጅ ፍላጎትን ለአቅርቦት ጋር ማጣጣም እንዳትችል አድርጓታል፡፡

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.