Logo
FastMereja
ደባርቅ የቱሪዝምና የልማት አቅሟን ወደ ተጨባጭ ውጤት ለመቀየር አዲስ የልማት ጉዞ ጀመረች

የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ መዳረሻ የሆነችው ደባርቅ ከተማ፣ ያላትን የተፈጥሮ፣ የታሪክና የቱሪዝም ሀብት በአግባቡ በመጠቀም ከተማዋን የተሻለ የቱሪዝምና የልማት ማዕከል ለማድረግ እና የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃት አዲስ የልማት እንቅስቃሴ ጀምራለች።

ደባርቅ በተፈጥሮ የታደለች ከተማ ከመሆኗ ባሻገር፣ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኘው ብርቅዬው ዋልያ፣ የተለያዩ የዱር እንስሳትና አእዋፋት እንዲሁም ሀገር በቀል እጽዋት የሚገኙበት የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ መግቢያ በመሆኗ ከፍተኛ የቱሪዝም አቅም አላት።

የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና ከተማ የሆነችው ደባርቅ፣ በራስ ደጀን ተራራና በሊማሊሞ ጠመዝማዛ መንገድ የተከበበች ሲሆን፣ በአካባቢዋ የሚገኙ የተፈጥሮና የቱሪዝም ሀብቶች ከከተማዋ አቅም ጋር ተጣጥመው እንዲለሙ የልማት ሥራዎች መጀመራቸው ተገልጿል።

በመላ ሀገሪቱ እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማትም ለደባርቅ ያላትን እምቅ አቅም ወደ ተጨባጭ የልማት ውጤት ለመቀየር ትልቅ ዕድል እንደሆነ ተጠቁሟል።

ይህንን የልማት ጉዞ ለማጠናከር የከተማዋ ነዋሪዎችም በሰላም ማስጠበቅ ላይ ያሳዩትን ተሳትፎ ወደ ልማት በማሸጋገር ንቁ ሚና እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል።

የደባርቅን የቱሪዝም አቅም፣ የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክንና በአካባቢው የሚገኙ ቅርሶችን ለመጠበቅና ለማልማት የሚያግዝ የምክክር መድረክም ተዘጋጅቷል።

“ቅርሶቻችንን እንንከባከብ፤ የወደፊታችንን እንገንባ!” በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደው ይህ መድረክ፣ ነሐሴ 18 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል ከ12፡00 ሰዓት እስከ ምሽት 2፡00 ሰዓት በታላቅ ድምቀት እንደሚካሄድ ተገልጿል።

በመድረኩ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ክቡር ታዬ አጽቀሥላሴ የክብር እንግዳ ሆነው እንደሚገኙ መረጃው ያመለክታል።

መድረኩ የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክንና ደባርቅን በማልማት፣ ቅርሶችን በመጠበቅና የአካባቢውን የቱሪዝም አቅም በማሳደግ ረገድ የሕዝብ፣ የተቋማትና የባለድርሻ አካላትን ትብብር ለማጠናከር የጋራ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያለመ ነው።

ደባርቅ ያላትን የተፈጥሮ፣ የታሪክና የቱሪዝም ፀጋ ከተገቢው ጥበቃና ልማት ጋር በማጣመር ወደ ዘላቂ የኢኮኖሚና የከተማ ልማት ለመቀየር የጀመረችው ጉዞ የከተማዋን ነገ የበለጠ ተስፋ ሰጪ ሊያደርግ እንደሚችል ተገልጿል።

በዚህ ጥረት የደባርቅ ተወላጆች፣ ነዋሪዎችና ደጋፊዎች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑም ተጠቁሟል።

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.