Logo
FBC
"ደቦ" የጥንቱ የኢትዮጵያውያን ትብብር ለዘመናዊው የአካባቢ ጥበቃ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያውያን በዚህ ክረምት የደቦ (ጅጌ) ሥራ አለባቸው፡፡ ሀገራቸው ደግሳ ልጆቿን ለብርቱ ሥራ ጋብዛለች - ለአረንጓዴ ዐሻራ፡፡

በተለያዩ የኢትዮጵያ ማሕበረሰቦች ባህል፣ የአንድነት፣ የደግነት፣ የትብብር እና የጋራ ጥንካሬ ትልቁ መገለጫ «ደቦ» ወይም በአንዳንድ አካባቢዎች «ጅጌ» ተብሎ የሚጠራው ሥርዓት ነው።

ይህ ከትውልድ ወደ ትውልድ የተሻገረ የጋራ የሥራ ባህል፣ ግለሰቦች ብቻቸውን ሊወጡት የማይችሉትን ከባድ የግብርና፣ የቤት ግንባታ እና የማኅበራዊ ሕይወት ፈተናዎች በአንድነት ለማሸነፍ የሚያስችል ጥንታዊ መፍትሔ ነው።

ዛሬ ላይ ይህ ታላቅ ማኅበራዊ እሴት አዲስ መልክና ብሔራዊ ግብ አንግቦ በኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ላይ በደመቀ ሁኔታ እየተተገበረ ይገኛል።

ይህን ጥንታዊ የማሕበረሰብ ዕውቀት ዛሬ ሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም. ከ805 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ችግኞችን በመትከል በወሳኝ ብሔራዊ ጉዳይ ላይ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡

ደቦ በባህሪው ለአንድ አምራች ወይም ባለሥራ ሳምንታት ሊፈጅ የሚችልን የአዝመራ ስብሰባ ወይም የአፈር ጥበቃ ሥራ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ በማጠናቀቅ ጊዜንና ጉልበትን ለመቆጠብ ያስችላል፡፡

ኢትዮጵያም በዚህ የክረምቱ ወቅት ልትተክል ያሰበችውን 8 ቢሊየን ችግኝ እቅድ ማሳካት የሚያስችላትን ከፍ ያለ ሥራ ከውናለች፡፡

ክረምቱ ከገባበት ጊዜ እንስቶ እስካሁን ድረስ 6 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞች የተተከሉ ሲሆን፣ ዛሬ በሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም ብቻ ከ805 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ችግኞችን በመትከል ከእቅድ በላይ ማሳካት ተችሏል፡፡

በሰዎች መካከል መተባበርን፣ መከባበርንና ማኅበራዊ ትስስርን የሚያጠናክረው የደቦ ሥርዓት አሁን በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ላይም ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎች ለሀገራቸው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በአንድ እንዲቆሙ አድርጓል፣ አስተባብሯልም፡፡

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በየዓመቱ በተሳካ ሁኔታ እንዲቀጥል ያደረገው ዋናው ሞተርም ይህ የቆየው የደቦ (ጂጌ) ባህል ነው።

በሚሊየን የሚቆጠሩ የተለያዩ የችግኝ ዝርያዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመትከል የመንግሥት መዋቅር ብቻውን በቂ ባለመሆኑ የጂጌ መንፈስ እንደ ዋና መፍትሔ ሆኖ አገልግሏል።

ልክ ለአዝመራ መሰብሰብ እንደምንሰባሰበው ሁሉ፣ ዛሬም የመንግሥት ሠራተኛው፣ አርሶ አደሩ፣ ተማሪዎቸ፣ የኃይማኖት መሪዎች፣ ሴቶች ፣ወንዶች ፣ህጻናቱ ሳይቀሩ በአንድነት ብርዱ እና ክረምቱ ቅዝቃዜ ሳይበግራቸው ወደ ችግኝ መትከያ ቦታዎች በመትመም ዐሻራቸውን አኑረዋል፡፡

ደቦ «የወንድሜ ሥራ የኔም ሥራ ነው» የሚል እሳቤ አለው። የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄም «የሀገር ስራ የሁሉም ትውልድ ሥራ ነው፣ ሀገር የሁሉም በመሆኗ አካባቢን የመጠበቅ ኃላፊነትም የጋራ ነው» የሚል ተመሳሳይ መርህን ይከተላል።

በችግኝ ተከላው ወቅት በአባቶች እናቶችና ወጣቶች ዘንድ የሚታየው የትብብር ትዕይንት ዕድሜ ጠገቡ የሀገር ቤት የደቦ ሥርዓት በትልልቅ ብሔራዊ መድረኮች ለትውልድ ግንባታ እየዋለ ለመሆኑ ጠቋሚ ነው፡፡

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በአንድ በኩል የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልና የሀገሪቱን የደን ሽፋን ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት ሲያግዝ በሌላ በኩል ደግሞ በቴክኖሎጂና በዘመናዊነት ምክንያት እየጠፋ የመጣውን የትብብር ባህል አዲሱ ትውልድ በተግባር እንዲማረውና እንዲረከበው በር ከፍቷል።

ባጭሩ የአረንጓዴ ዐሻራ ስኬት የኢትዮጵያውያን ጥንታዊ የደቦ ባህል ዛሬም ሕያው መሆኑን እና ለዘመናዊ ዓለም አቀፋዊ ችግሮች እንደ አካባቢ መራቆት ያሉ ፈተናዎች ሀገር በቀል መፍትሔ መሆን እንደሚችል ያሳየበት ታላቅ ማረጋገጫ ነው።

ኢትዮጵያም ባለፉት 7 ዓመታት ልጆቿን አሰባስባ ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞችን ተክላለች፡፡ በዛሬው ዕለት ደግሞ በአንድ ጀምበር ልጆቿን ደቦ ጠርታ ከ805 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ችግኞችን መትከል ችላለች፡፡

በእመቤት ሲሳይ

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.