Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) በመጪው መስከረም ይፋ ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ረቂቅ ሪፖርት፣ ከአሜሪካዊ የጦር ተቋራጭ ጋር ግንኙነት ያላቸው ቦይንግ 727 አውሮፕላኖች ለሱዳኑ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል የጦር መሳሪያዎችን፣ ድሮኖችን እና የውጭ ቅጥረኛ ወታደሮችን ሲያመላልሱ መቆየታቸውን አጋለጠ። በዳርፉር ክልል የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽሟል ተብሎ በሚወነጀለው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል የጀርባ ደጋፊዎች ላይ ብርሃን የፈነጠቀው ይህ ሪፖርት፣ የውጭ ኃይሎች በሱዳን ጦርነት ውስጥ ያላቸውን ድብቅ እጅ እርቃኑን ያወጣ ነው።

ሮይተርስ ያገኘው ይህ የባለሙያዎች ሪፖርት እንደሚያስረዳው፣ እነዚህ አውሮፕላኖች ሆን ብለው ከራዳር እይታ ለመሰወር ጥረት ያደርጉ ነበር። ከቻድ መዲና ንጃሜና ወታደራዊ አየር ማረፊያ በመነሳት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ዋነኛ የጦር እና የሎጂስቲክስ ማዕከል ወደሆነችው የዳርፉሯ ኒያላ ከተማ በምሽት ሚስጥራዊ በረራዎችን ሲያካሂዱ ቆይተዋል። የቻድ መንግስት በሱዳን ጦርነት ውስጥ እጄ የለበትም፤ አላማዬ ሰላም ማምጣት ነው ቢልም፣ አውሮፕላኖቹ የቻድን አየር ማረፊያ መጠቀማቸው የቀጠናውን የጸጥታ ችግር ይበልጥ ውስብስብ እና የሀገሪቱን ፖለቲካዊ ግብዝነት ያጋለጠ አድርጎታል።

ከጦር መሳሪያ አቅርቦቱ ባሻገር ሪፖርቱ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች መሰረት ባለው 'ግሎባል ሴኪዩሪቲ ሰርቪስስ ግሩፕ' የተባለ ኩባንያ አማካኝነት የተቀጠሩ ከ1,500 እስከ 2,000 የሚደርሱ ኮሎምቢያውያን ቅጥረኛ ወታደሮች ለፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ድጋፍ መስጠታቸውን አጋልጧል። "የበረሃ ተኩላዎች" በመባል የሚታወቁት እነዚህ ቅጥረኞች፣ ድሮኖችን በማብረር እና የጦር ስልቶችን በመንደፍ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እ.ኤ.አ በ2025 በዳርፉር አል-ፋሽር ከተማ ያደረገውን ዘግናኝ ጥቃት መምራታቸው ተገልጿል። ይህ ጥቃት በተመድ "የዘር ማጥፋት" ወንጀል ተብሎ የተፈረጀ ሲሆን፣ ኤሚሬቶች ግን በበኩሏ የተጠቀሰው ኩባንያ ምንም ዓይነት የቅጥረኛ ወታደር ስምሪት አላደረገም ስትል አስተባብላለች።

ይህ ሪፖርት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሃንን የገደለው እና በዓለማችን እጅግ የከፋውን ሰብዓዊ ቀውስ የፈጠረው የሱዳን ጦርነት፣ ከጀርባ በውጭ ኃይሎች የጦር መሳሪያ እና የቅጥረኛ ወታደሮች አቅርቦት እንዲሁም በሚስጥራዊ በረራዎች እንዴት እየተቀጣጠለ እንደሚገኝ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው።

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.