Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) የሜታ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ማርክ ዙከርበርግ፣ በዓለማችን ከፍተኛ ዋጋ ካላቸው የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኩባንያዎች መካከል የሆኑትን አንትሮፒክ እና ኦፕን ኤአይ የኤአይ ቴክኖሎጂን የሚያለሙበትን የተዘጋ መንገድ አጥብቀው ተቹ። ዙከርበርግ ይህ ዓይነቱ አካሄድ ስልጣንና ኃይልን በአንድ ማዕከል እንዲከማች እንደሚያደርግና ሰዎች ከዚህ ለውጥ አምጪ ቴክኖሎጂ የሚያገኙትን ተጠቃሚነት እንደሚያጠብ አስጠንቅቀዋል።

የ42 ዓመቱ ዙከርበርግ ማክሰኞ ዕለት ከኒውዮርክ ታይምስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ የኩባንያዎቹን ስም በቀጥታ ባይጠቅሱም፤ ግንባር ቀደም የጥናት ተቋማት የኤአይ ቴክኖሎጂን በጥብቅ ቁጥጥር ስር ለማልማት የሚያደርጉት ጥረት የአሜሪካን የቴክኖሎጂ እሴቶች ከመተው ጋር እኩል መሆኑንና ፈጠራን እንደሚያዳፍን ገልጸዋል። በዘርፉ "ከመጠን ያለፈ የጥፋት ትርክት" እንደሚስተዋል የገለጹት ዙከርበርግ፣ ለውይይቱ "እውነታን" የሚያመጡ ድምጾች እንደሚያስፈልጉ አሳስበዋል።

በሲሊከን ቫሊ የተፈጠረው የሐሳብ ልዩነት የዙከርበርግ አስተያየት በሲሊከን ቫሊ የቴክኖሎጂ መሪዎች መካከል የተፈጠረውን ክፍፍል ይበልጥ አጉልቶታል። የአንትሮፒክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዳሪዮ አሞዴይ እና የኦፕን ኤአይ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሳም አልትማን የኤአይ ሞዴሎች እጅግ አደገኛ በመሆናቸው ያለ ጥብቅ ቁጥጥር ሊለሙና ሊጋሩ አይገባም የሚል አቋም አላቸው። በሌላ በኩል ማይክሮሶፍት፣ ኤንቪዲያ (Nvidia)፣ ጉግል እና ሜታ ይህንን ሀሳብ በመቃወም፣ ቴክኖሎጂው እንዲያድግ እና አዳዲስ የንግድ ዘርፎች እንዲፈጠሩ አብዛኛዎቹ የኤአይ ሞዴሎች በክፍት መንገድ መለማት አለባቸው ብለው ይከራከራሉ።

የቻይና ስጋት እና የዋሽንግተን ሎቢ በዚህ ወር የቻይና የኤአይ ሞዴሎች ያሳዩት ፈጣን እድገት የአሜሪካ ኩባንያዎች የነበራቸውን ብልጫ እየቀነሰው መምጣቱ ክርክሩን አባብሶታል። አርብ ዕለት የኤንቪዲያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጄንሰን ሁዋንግ ክፍት የሶፍትዌር ልማትን የሚደግፍ ደብዳቤ ያወጡ ሲሆን፣ ከ SpaceX እና IBM ጋር በመሆን በክፍት የኤአይ ደህንነት ላይ የሚሰራ ጥምረት ማቋቋማቸውን ይፋ አድርገዋል። ሁዋንግ እና አልትማንን ጨምሮ የቴክኖሎጂ መሪዎች ጉዳዩን ከትራምፕ አስተዳደር ጋር ለመወያየት በዚህ ሳምንት ወደ ዋሽንግተን እያቀኑ ይገኛሉ።

"ግላዊ ሱፐር-ኢንተለጀንስ" ከማዕከላዊ ቁጥጥር ይልቅ አንትሮፒክ የኤአይ ሞዴሎች ለሰው ልጅ ደህንነት ስጋት እንዳይሆኑ "የአሰላለፍ አደጋን" ለመፍታት ሲሞክር፤ ዙከርበርግ ግን አንድ ወጥ የሆነ እና ለሁሉም በእኩል የሚስማማ "ደግ" ሱፐር-ኢንተለጀንስ መፍጠር ፈጽሞ የማይቻል መሆኑን ይከራከራሉ። በምትኩ የሰዎችን ግላዊ ፍላጎት ሊያሟላ የሚችል "ግላዊ ሱፐር-ኢንተለጀንስ" ለሁሉም ሰው መድረስ አለበት ብለዋል።

ለዓመታት የኦፕን ኤአይ አቀንቃኝ የነበረችው እና ሞዴሎቿን በነጻ ስታድል የቆየችው ሜታ፣ በቅርቡ የስትራቴጂ ለውጥ አድርጋለች። በአንትሮፒክ እና ኦፕን ኤአይ ተቀድማ የነበረችው ሜታ፣ 14.3 ቢሊዮን ዶላር ScaleAI በተባለ ኩባንያ ላይ ኢንቨስት በማድረግ እና መስራቹን አሌክሳንደር ዋንግን በመቅጠር 'Meta Superintelligence Labs'ን አቋቁማለች። ኩባንያው 'Muse Spark' የተሰኘ አዲስ ዝግ (Closed) ሞዴል በማልማት በዚህ ወር መሸጥ መጀመሩም ተገልጿል፤ ምንም እንኳ የክፍት ሞዴል ልማቱን ጎን ለጎን እያስኬደ ቢሆንም።

ዙከርበርግ በዎል ስትሪት ጆርናል ላይ ባወጡት ጽሁፍ የኤአይ ኃይል ማዕከላዊነትን አጥብቀው በመንቀፍ፣ የኢንዱስትሪው ታሪካዊ ጉዞ የቴክኖሎጂን ኃይል በጥቂቶች እጅ ከመሰብሰብ ይልቅ ክፍት በማድረግ ወደ ብዙሃኑ እጅ ማስገባት መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል። ተቀናቃኞቹ አንትሮፒክ እና ኦፕን ኤአይ በበኩላቸው የኤአይ ልማት ደህንነትን ለማረጋገጥ ዓለም አቀፍ ትብብር እንዲኖር የሚጠይቅ ግልጽ ደብዳቤ ከሌሎች ተመራማሪዎች ጋር ፈርመው አውጥተዋል።

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.