Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ሕይወት) ይህን ዘገባ ትናንት በቪዲዮ አቅርበነው ነበር፤ ብዙዎቻችሁ፣ 'ኢንተርኔት ፍጥነት በሌለባቸው አካባቢዎች ቪድዮ ለማየት ስለሚቸገሩ' በጽሑፍ ይቅረብልን ባላችሁን መሠረት እንደሚከተለው ቀርቧል | ወዳጅነት... ከለላና መሸሸጊያ ይሆናል ተብሎ ይታሰባል፤ ለዲዛይነር ቅድሳን ይርጋለም ግን ወዳጅነት የሞት ወጥመድ ሆኖ አረፈው። የ2026ቱ የ"ሚስ ወርልድ ኢትዮጵያ" የውበት ንግሥት የሩት ይርጋለም ታላቅ እህት የሆነችው ቅድሳን፣ በሞዴሊንግ ዓለም ውስጥ ስኬትን ከምትመኘውና ከእህቷ ጋርም የትምህርት ቤት ትውውቅ ከነበራት ቅድስት ሙሉቀን ጋር የጠበቀ ጓደኝነት ነበራት። ሆኖም ከዚህ ጓደኝነት ጀርባ፣ ጥልቅ የሆነ ምቀኝነት እና አደገኛ ሴራ ተሸሽጎ ነበር።

ሁሉም ነገር የተጀመረው አርብ ዕለት በተደረገ አንድ የስልክ ጥሪ ነው። ለአንድ ዓመት ያህል ተጠፋፍታ የነበረችው ቅድስት፣ የናፍቆት በሚመስል የጓደኝነት መንፈስ ለቅድሳን ደወለች። "አዲስ ኮንዶሚኒየም ተከራይቻለሁ፤ መጥተሽ ቤቴን እዪልኝ። ደግሞም የማገናኝሽ አዲስ የስራ እድል አለ" በማለት የጓደኛዋን ልብ አባበለች። በጓደኛዋ ላይ አንዳችም ክፋት ያልጠረጠረችው ቅድሳን፣ ሜክሲኮ አካባቢ ተገናኝተው አብረው ወደ ኮዬ ፈጬ ኮንዶሚኒየም አመሩ። ቅድሳን የጓደኛዋን አዲስ ሕይወት ለማየት በደስታ ስትጓዝ፣ እየሄደች ያለችው ግን ወደራሷ የሞት ቀጠሮ ነበር።

አዲሱ ቤት ደጃፍ ላይ ደርሰው ወደ ውስጥ ሲገቡ፣ የነበረው ወዳጃዊ ድባብ ቅጽበታዊ በሆነ ሽብር ተተካ። ቤት ውስጥ አድፍጦ ይጠብቅ የነበረው የቅድስት ፍቅረኛ ደሳለኝ፣ ቅድሳን ድምጿን አውጥታ እንኳ ርዳታ እንዳትጠራ አፍኖ አሰራት። ያመነቻት ጓደኛዋ እጅ ከፍንጅ ለሞት አሳልፋ ሰጠቻት።

አጋቾቹ ወዲያውኑ የሟች ቤተሰቦች ጋር በመደወል የሁለት ሚሊዮን ብር ቤዛ ጠየቁ። የቤተሰብ ልብ በጭንቀት እየመታ የድርድር ሀሳቦች ሲለዋወጡ፣ አጋቾቹ አንድ ዘግናኝ እውነት ተገነዘቡ። የጠየቁትን ገንዘብ ቢያገኙ እንኳ፣ ሟች በቅርበት ስለምታውቃቸው ነገ ሚስጥራቸውን አሳልፋ እንደምትሰጣቸው አሰቡ። ፍርሃት እና ምቀኝነት ያደነደነው ልባቸው፣ እዚያው አርብ ዕለት ጭካኔ የተሞላበት ውሳኔ ላይ ደረሰ። የቅድሳንን ሕይወት በአሰቃቂ ሁኔታ አጠፉ። አስከሬኗንም ማንም እንዳያገኘው በሚል እዚያው አካባቢ በተከራዩት ሌላ ተጨማሪ ቤት ውስጥ ደበቁት።

ይሁን እንጂ...የፈጸሙት ግፍ በጨለማ ሊቀበር አልቻለም። ፖሊስ ባደረገው አፋጣኝ እና የተቀናጀ ክትትል፣ ዋነኛ ተጠርጣሪዋ ቅድስት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ጎተራ አካባቢ በቁጥጥር ስር ዋለች። የወንጀሉ ተባባሪ የነበረው ደሳለኝ ደግሞ፣ ሁኔታው ሲከፋበት ለማምለጥ ሞክሮ አዳማ ከተማ ውስጥ ተደብቆ እያለ በፖሊስ መረብ ውስጥ ወደቀ። በአጠቃላይ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ስምንት ሰዎች ታሰሩ። ዋነኛ ተጠርጣሪዎቹም ወንጀሉን መፈጸማቸውን አምነው፣ እንዴት እንዳከናወኑት በቦታው ተገኝተው ለፖሊስ አሳይተዋል።

ይህ ክስተት የ2026ቷን የውበት ንግሥት ሩትን ብቻ ሳይሆን፣ መላውን ማኅበረሰብ በሐዘን እና በስጋት ውስጥ ጥሏል። ሩት በልብ ስብራት "ከጠላቴ እኔ እጠነቀቃለሁ፤ ከወዳጄ አንተ ጠብቀኝ" ብላ ያሰፈረችው መልእክት፣ የዚህን ትረካ አሳዛኝ ማጠቃለያ ይወክላል፦ ጠላት ፊቱን አውቆ ሲመጣ፣ ክህደት ግን በወዳጅ ፈገግታ ታጅቦ ይመጣል።

3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.