Logo
EBC
የዓድዋ ገድል በአረንጓዴ አሻራ ሲደገም
*****************

በኢትዮጵያ እየተተገበረ የሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሀገርን የተፈጥሮ ሀብት ከመጠበቅ ባሻገር፣ ሉዓላዊነትን የማስከበር ዋነኛ ማሳያ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) በ2018 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ማስጀመሪያ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ሉዓላዊነት በሁለት መንገዶች ሊደፈር እንደሚችል ማንሳታቸው ይታወሳል።

የመጀመሪያው በውጭ ወራሪ ሀይል በኩል ድንበር ጥሶ በመግባት የሚፈጸም ሲሆን፤ ይህንንም ኢትዮጵያውያን በዓድዋ ጦርነትና በሌሎችም አውዶች በደም መስዋዕትነት አስጠብቀዋል።

ሁለተኛውና ጸጥተኛው የሉዓላዊነት መደፈር ግን፣ እንደ አፈር ያለ ወደፊት በቀላሉ የማይተካ ውድ የተፈጥሮ ሀብት በጎርፍና በመሸርሸር ድንበር አቋርጦ ሲወጣ የሚከሰት ነው።

የሚሸረሸር አፈር፣ የሚደርቅ ሀይቅ፣ የሚጠፋ ደን፣ እንዲሁም የሚመናመን የምግብ ዋስትና በዝምታ የሚፈጸሙ የሉዓላዊነት መሸርሸር ማሳያዎች ናቸው።

ለዘመናት በውሃና በንፋስ ምክንያት ሲጠፋ የነበረው ለም አፈር የገበሬውን ምርት፣ የምግብ ዋስትናን፣ የወደፊቱን ኢኮኖሚ እንዲሁም የትውልድን ተስፋ አብሮ ይዞ የሚወጣ በመሆኑ፤ የአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴ ይህንን ጸጥተኛ ወረራ የመቀልበስ ሀገራዊ ስትራቴጂ ሆኖ እየተተገበረ ይገኛል።

ይህ መርሃ ግብር ለአካባቢ ጥበቃ ብቻ ሳይሆን፣ ከፍተኛ የገበያ ዋጋ ያላቸውን እንደ ቡና፣ አቮካዶ፣ ማካዴሚያ፣ ካካዎ እና ሮማን የመሳሰሉ ሰብሎችን በማስፋፋት ለውጭ ምንዛሬ ግኝትና ለስራ እድል ፈጠራ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።

በተጨማሪም ሀይቆች ሲያገግሙ፣ አእዋፋት ወደ መኖሪያቸው ሲመለሱና ደኖች ሲለሙ ለኢኮ-ቱሪዝም መስፋፋት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ሲሆን ይህም በዜጎች ገቢና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ጉልህ አዎንታዊ ለውጥ እንዲመጣ ያስችላል።

የዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ የተጀመረባት ቢሾፍቱ፣ እስከ አዋሽ ያለው ቀጠና የሀይቆች ስርዓት የአእዋፍ ብዝሃ ሕይወትና የተፈጥሮ ገጽታ ለኢኮ ቱሪዝም ትልቅ እምቅ አቅም እንዳለው ያሳያል። ተፈጥሮ ሲጠበቅ ቱሪዝም ያድጋል፤ ቱሪዝም ሲያድግ ደግሞ ለዜጎች ሥራ፣ ገቢና ኢኮኖሚያዊ እድል ይፈጥራል።

ትውልድ በታሪክ የሚታወሰው የሠራው ስራ በሚያስቀረው ውርስ ነው። የዓድዋ ትውልድ ነፃነትን አውርሶናል፤ የዛሬው ትውልድ ደግሞ አረንጓዴ ኢትዮጵያን የመተው ኃላፊነት አለበት። የሚተከለው ችግኝ ዛሬ ትንሽ ቢመስልም ነገ የልጆቻችን ጥላ፣ ሀብት፣ ምግብ፣ ቱሪዝምና የአገር ክብር ይሆናል።

የአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴ የችግኝ ተከላ ብቻ አይደለም፤ የሉዓላዊነት ጥበቃ፣ የኢኮኖሚ ማንሰራራት፣ የምግብ ዋስትና፣ የቱሪዝም እድገት፣ የአካባቢ ጥበቃና የትውልድ ውርስ በአንድ ላይ የሚገናኙበት ሀገራዊ እንቅስቃሴ ነው።

የአባቶቻችን ገድል ነፃነትን አስጠብቆልናል፤ የዛሬው አረንጓዴ ገድል ደግሞ ያንን ነፃነት በለምለም ምድር፣ በበለጸገ ኢኮኖሚና በዘላቂ ልማት ለቀጣዩ ትውልድ የማስረከብ ታሪካዊ ኃላፊነት ነው።

በልዩ እሸቱ

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.