Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ስፖርት) የዓለም ዋንጫው ግለት ጣሪያ ነክቷል! ረቡዕ ዕለት በአትላንታ ስታዲየም (ቢትዮጵያ አቆጣጠር ምሽት) በሚካሄደው የዓለም ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ታላቅ ፍጥጫ፣ የአምናዋ ሻምፒዮኗ አርጀንቲና ከእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን ጋር ስትፋጠጥ ታዋቂውን ጥቁር ሰማያዊ የሜዳ ውጪ ማልያዋን አጥልቃ ወደ ሜዳ እንደምትገባ ታውቋል። በበኩሏ እንግሊዝ ሙሉ ነጭ የሆነውን የሜዳዋን ማልያ ለብሳ ለዚህ ትልቅ ጦርነት ትቀርባለች።

አርጀንቲና በዘንድሮው ውድድር ይህንን ማልያ የተጠቀመችው በምድብ ድልድሉ ጆርዳንን 3 ለ 1 ባሸነፈችበት ጨዋታ ላይ ብቻ ነው። ይሁን እንጂ... ይህ የማልያ ምርጫ ከፊፋ የደንብ አሰራር ባሻገር ትልቅ የስነ-ልቦና እና የ"እምነት" ሚስጥር እንዳለው በአርጀንቲና ሚዲያዎች በስፋት እየተነገረ ይገኛል። ምክንያቱም ይህ ጠቆር ያለ ሰማያዊ ማልያ፣ አርጀንቲናውያን በእንግሊዝ ላይ ታሪካዊ ድል ለተቀዳጁባቸው የ1986ቱ እና የ1998ቱ የዓለም ዋንጫዎች ትልቅ ትዝታ ያለው በመሆኑ ነው!
በተለይም በ1986ቱ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና በታሪካዊቷ "የአምላክ እጅ" ጎል እንግሊዝን 2 ለ 1 ሲያሸንፉ፣ እንዲሁም በ1998ቱ የፈረንሳይ ዓለም ዋንጫ የጥሎ ማለፍ (Last-16) ጨዋታ በፔናሊቲ መለያ ምት የሶስቱን አናብስት ስብስብ ሲያሸንፉ ያጠለቁት ይሄንኑ ማልያ ነበር።

በተቃራኒው ግን በ2002ቱ በጃፓን በተካሄደው የዓለም ዋንጫ የምድብ ጨዋታ እንግሊዝ ቀይ ማልያ ለብሳ፣ አርጀንቲና ደግሞ ባህላዊውን ባለ መስመር ማልያዋን ለብሳ በተገናኙበት ጨዋታ እንግሊዝ 1 ለ 0 ማሸነፏ የማይዘነጋ ነው።

የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) አሰራር እያንዳንዱ ቡድን የሜዳውን የመጀመሪያ ምርጫ ማልያ እንዲለብስ ቅድሚያ የሚሰጥ ቢሆንም፣ የማልያ ቀለም መመሳሰል ካጋጠመ ግን የለቀቀ እና የደመቀ ቀለም እንዲኖር እርምጃ ይወስዳል። ይህም በተለይ colour blindness ችግር ላለባቸው ደጋፊዎች ጨዋታውን በቀላሉ እንዲከታተሉ ታስቦ የሚደረግ ጥንቃቄ ነው።

ወደዚህ ግዙፍ የግማሽ ፍጻሜ ጦርነት ለመድረስ ሁለቱም ቡድኖች ፈታኝ መንገድ አልፈዋል። እንግሊዝ ባለፈው ቅዳሜ ኖርዌይን በጭማሪ ሰዓት 2 ለ 1 ስታሸንፍ፤ አርጀንቲና ደግሞ እሁድ ዕለት 10 ተጫዋቾች ብቻ ቀርተውባት ከነበረችው ስዊዘርላንድ ጋር ባደረገችው እጅግ አጓጊ ጨዋታ በጭማሪ ሰዓት 3 ለ 1 አሸንፋ ማለፏ ይታወቃል። አሁን የዓለም እግር ኳስ አፍቃሪዎች ዓይን በአትላንታው የረቡዕ ምሽት ፍልሚያ ላይ አርፏል!

3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.