Logo
FBC
ሰላም፤ እንደምን አደራችሁ?

ሌብነትና ሙስናን ለማስቀረት በርካታ ርምጃዎችን የወሰደው መንግሥት …

ስር የሰደደ፣ ህዝብ ያማረረና ለሀገር የደህንነት ስጋት የሆነውን ሙስና ለመግታት መንግሥት ብሔራዊ የጸረ ሙስና ኮሚቴ እስከማቋቋም የደረሰ ርምጃ መውሰዱ ይታወሳል፡፡

ሌብነት (ሙስና) በመንግሥት ተቋማት ዘንድ እንደሚዘወተር በብዛት ቢገለጽም ከአነስተኛ ሀገር በቀል እስከ ድንበር ተሻጋሪ ኩባንያዎች እና በግል ድርጅቶችም ጭምር የከፋ እንደሆነ ጥናቶች ይጠቁማሉ።

ሙስና በኢትዮጵያ ከኑሮ ውድነትና ስራ አጥነት ቀጥሎ የሀገር ደህንነት ስጋት መሆኑ በመንግሥት ይፋ ሆኗል።

ጥናቶች ሙስናን በተለያዩ ደረጃዎችና መልኮች የሚገልጹት ሲሆን፤ መጠነ ሰፊ ሙስና፣ አነስተኛ ሙስና፣ ፖለቲካዊ ሙስና እና ስልታዊ ሙስና በሚል ይመደባሉ።

ሙስና ድህነትን ያባብሳል፤ ሰብዓዊ መብትና ክብርን ይገፋል፤ አካባቢን ይሸረሽራል፤ ዕድገትን ይጎትታል፤ ውስጣዊና በሀገራት መካከል ግጭት ይቀሰቅሳል፤ የመንግሥትን ቅቡልነት እና ዴሞክራሲን ይፈታተናል።

ሙስና ጠንክሮ መስራትን የሚኮንን፣ ሳይሰሩ መብልጸግን የሚያጀግን፣ የአጋርነትን ሞራል የሚሰብር፣ ሀገርን ለውጫዊ ደህንነት ስጋት የሚጥል፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን የሚያቀጭጭ፣ ውስጣዊ ስርዓትና መረጋጋትን የሚፈትን፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እና አጠቃላይ ዘላቂ ልማትን የሚገታ ክፉ ነቀርሳ ነው።

እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊ ሀገራት ደግሞ ሙስና በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኗል።

በመንግሥት አግልግሎት አሰጣጥ፣ በመሬት አስተዳደር፣ በፋይናንስና ግዥ፣ በመሰረታዊ ፍጆታ አቅርቦት ዘርፎች ላይ በስፋት የሚስተዋለውን ሙስና ለማስቀረት መንግሥት ዲጂታላይዜሽንን ከማስፋፋት ጀምሮ በርካታ ስራዎችን ሰርቷል፡፡

በፀጥታና ፍትህ ተቋማት ዘንድም ኃላፊነትን ያለአግባብ በመጠቀም በአቋራጭ የመበልፀግ የሙስና ወንጀሎችን ለማስወገድ መንግሥት ያለርህራሄ ርምጃ እንደሚወስድ በተደጋጋሚ አስታውቋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ ሌብነት ጥዩፍ እና ቆሻሻ ነገር መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

ከሌብነት ጋር በተያያዘ ብዙ እንደሚባል ጠቅሰው፤ ተጠያቂ ለማድረግ ሰዉ ማስረጃ የማቅረብ ክፍተት እንዳለበት አመልክተዋል።

ሰው እንደሚፎክረው አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አንድ ሰው የተጣራ የኦዲት ሪፖርት አምጥቶ መንግሥት ርምጃ አልወሰደም ካለ እኔ ኃላፊነት እወስዳለሁ በማለትም መንግሥት ጉዳዩን አጥብቆ እንደሚዋጋው አረጋግጠዋል።

ሌብነትን ስም ማጥፊያ ከማድረግ በዘለለ በተጨባጭ ማስጠየቅ የሚያስችል ጉዳይ ማቅረብ ከተቻለ መንግሥት ርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑን ጠቅሰው፤ መንግሥትና ህዝብ አደራ ብሏቸው ቃለ መሓላ ፈጽመው ከዚህ ምስኪን ህዝብ የሚያጭበረብሩ እንዳሉም ጠቁመዋል።

ሌብነት ክፉ መሆኑን አምነን መጀመሪያ ራስን መታገል አልፎ ሲሄድ ደግሞ በህግ የሚያስጠይቅ ማስረጃ መያዝ ጠቃሚ ይሆናል ነው ያሉት።

3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.