Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝደንት በጋና ሊያደርጉት ያቀዱት ጉብኝት መሰረዙ ተዘገበ፡፡ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎዛ በሚቀጥለው ወር ማለትም በኦገስት የመጀመሪያው ሳምንት ባሉት ቀናት በጋና ጉብኝት ለማድረግ የሚያስችል ፕሮግራም ተይዞላቸው ነበር፡፡ ይህ ጉብኝት በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ መሆኑም ተገልጿል፡፡ ይሁንና የጋና መንግስት ይህንን ፕሮግራም መሰረዙን ሰሀራ ሪፖርተርስ ዘግቧል፡፡

እንደዘገባው ጉብኝቱ የተሰረዘው በደቡብ አፍሪካ ውስጥ በስደተኞች ላይ ባነጣጠረው ጥቃት አንድ ጋናዊ መገደሉ በሁለቱ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ውጥረት በመፍጠሩ ነው፡፡ የጋና መንግስት ጁን 30 በኬፕ ታውን በተደረገው መጤ ጠል የተቃውሞ ሰልፍ ወቅት የ40 አመቱ ባሽሩ ኢሳክ የተባለ ዜጋው መገደሉን አስታውቋል፡፡ የአክራ ባለስልጣናት እንደሚገልፁት የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝደንት ጉብኝት ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ የተደረገ ሲሆን ይህም በዚያ የሚገኙ ዜጎቻቸው ደህንነት እንዳሰጋቸው የሚያሳይ ምልክት ነው፡፡

ባለስልጣናቱ በውጭ አገር የሚገኙ ጋናዊያንን ደህንነት ማረጋገጥ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ የጋና መንግስት የዜጋውን ግድያ በተመለከተ ለደቡብ አፍሪካ መንግስት በይፋ ተቃውሞ ያቀረበ ሲሆንም ደቡብ አፍሪካ ግን ጁን 30 በነበረው ተቃውሞ የተገደለ ምንም ሰው እንደሌለ በመናገር ላይ ናት፡፡ የደቡብ አፍሪካ የፍትህ ሚኒስትር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ‹‹የጋና ባለስልጣናት ስለደቡብ አፍሪካ የተሳሳተ መረጃ እያሰራጩ ነው›› በማለት መግለፃቸውም ይታወሳል፡፡

3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.