Logo
EBC
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ5 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
*******************

በኢትዮጵያ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት ከ5 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች በሰጡት ምላሽ እና ማብራሪያ ገልጸዋል።

ከእነዚህ መካከል 4.9 ሚሊዮን የሚሆኑት በሀገር ውስጥ የሥራ ዕድል ያገኙ ሲሆኑ፣ ከ101 ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ በውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት ተጠቃሚ የሆኑ ናቸው።

በተጨማሪም በልዩ የክህሎትና ሙያ ዘርፍ የተሰማሩ 40 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል ማግኘታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።

የየዘርፉን የሥራ ዕድል ፈጠራ ድርሻ በተመለከተም፥ ግብርና ከ2 ሚሊዮን በላይ፣ አገልግሎት፣ ንግድ እና ዲጂታላይዜሽን 1.8 ሚሊዮን እንዲሁም ኢንዱስትሪ ከ900 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን አብራርተዋል።

የሥራ ዕድል ፈጠራ አፈጻጸም በሀገር ውስጥ የ13 በመቶ እንዲሁም በውጭ ሀገራት ስምሪት የ27 በመቶ ዕድገት ያሳየ መሆኑን አክለው ገልጸዋል።

የፋይናንስ ዘርፉ በዲጂታላይዜሽን መታገዙ ያመጣውን ከፍተኛ ለውጥ ተከትሎ የሀገራችን አጠቃላይ ቁጠባ ከነበረበት 2.6 ትሪሊዮን ብር አሁን ላይ ወደ 4 ትሪሊዮን ብር ገደማ መድረሱን ተናግረዋል።

አዲሱ የውጭ ምንዛሬ ፖሊሲ ተግባራዊ ከሆነ ወዲህ የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ባንክ ገበያውን ለማረጋጋት 2.7 ሚሊዮን ዶላር ለገበያ ማቅረቡንና የፋይናንስ ዘርፉ በአሁኑ ወቅት በትሪሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ የሚንቀሳቀስበት ግዙፍ ሴክተር መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።

በበረከት ሽመልስ
#ethiopia #parliament #pmabiyahmed #employment #ebc

3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.