Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ስፖርት) ዛሬ በቦስተን ስታዲየም የዓለማችን ምርጦቹ ሁለት አጥቂዎች ፊት ለፊት ሲገናኙ የእግር ኳስ አፍቃሪው አይን ሁሉ ወደዛው ያመራል። ፈረንሳይ ከኪሊያን ኤምባፔ ጋር፣ ኖርዌይን ከኤርሊንግ ሃላንድ ጋር ታፋልማለች! ሁለቱም ሀገራት በኮከብ አጥቂዎቻቸው አስደናቂ ብቃት ታግዘው የምድባቸውን የመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎች በድል አጠናቀዋል። ኤምባፔ እና ሃላንድ በሁለቱ ጨዋታዎች እያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ግቦችን በማስቆጠር በአጠቃላይ 4 ግቦችን አስመዝግበው ውድድሩን አሙቀውታል። በአሁኑ ሰዓት ሊዮኔል ሜሲ በ5 ግቦች የኮከብ ግብ አግቢነቱን እየመራ ይገኛል።

ሁለቱም ሀገራት ወደ ጥሎ ማለፉ ማለፋቸውን ቢያረጋግጡም፣ የምድብ 9 (Group I) አንደኛ ሆኖ ለማጠናቀቅና በጥሎ ማለፉ የተሻለ ተጋጣሚ ለማግኘት ሲሉ ሁለቱም ኮከቦች በቋሚነት ይሰለፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ይህን ልብ አንጠልጣይ ፍልሚያ ከመመልከታችን በፊት፣ ቢቢሲ ስፖርት ተጫዋቾቹ ለሀገራቸው ያላቸውን ፋይዳ እንደሚከተለው ዳስሶታል።

በክለቦቻቸው ያላቸው ወሳኝነት እንዳለ ሆኖ፣ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ የሁለቱ ተጫዋቾች ተጽእኖ እጅግ የገዘፈ ነው። ከነሐሴ 2022 ጀምሮ ፈረንሳይ ኤምባፔን አሰልፋ 69.8% ጨዋታዎቿን ስታሸንፍ፣ እርሱ በሌለበት ግን የማሸነፍ መጠኗ ወደ 50% ይወርዳል። የምንጊዜም የፈረንሳይ ከፍተኛ ግብ አግቢው ኤምባፔ በሜዳ ላይ ሲኖር ፈረንሳይ በጨዋታ በአማካይ 2.3 ግቦችን ስታስቆጥር፣ በሌለበት ደግሞ 1.9 ግቦችን ታስቆጥራለች። በሌላ በኩል ኖርዌይ ያላት የተጫዋቾች ስብስብ ጥልቀት አነስተኛ በመሆኑ፣ ሃላንድ ለሀገሩ ያለው ወሳኝነት ከማንም በላይ ነው። ከነሐሴ 2022 ጀምሮ ኖርዌይ ሃላንድን አሰልፋ 64.5% ጨዋታዎቿን ስታሸንፍ፣ እርሱ በሌለበት ግን የማሸነፍ መጠኗ በከፍተኛ ሁኔታ ወደ 33.3% ይንኮታኮታል።

ይህ የዓለም ዋንጫ ሁለቱም ተጫዋቾች በትልልቅ መድረኮች ጫና እንደማይበገሩ በሚገባ አሳይቷል። ትኩረቱ ሁሉ በሜሲ ላይ ቢሆንም፣ ኤምባፔ የዓለም ዋንጫ የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አግቢነት ሪከርድን ለመስበር የጊዜ ጉዳይ ብቻ የሆነለት ይመስላል። በ16 የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች 16 ግቦችን ያስቆጠረው ፈረንሳዊው ኮከብ፣ ከ39 ዓመቱ ሜሲ የሚያንሰው በሁለት ግቦች ብቻ ነው። ኤምባፔ ከሜሲ በ12 ዓመት ማነሱ ደግሞ ሪከርዱን በእጁ ለማስገባት ሰፊ እድል ይሰጠዋል።

በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ የመጀመሪያ ተሳትፎውን እያደረገ ያለው ሃላንድ በበኩሉ፣ ውድድሩን እንደለመደው እያመሰቃቀለው ይገኛል። በመጀመሪያዎቹ ሁለት የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች ከአንድ በላይ ግቦችን ያስቆጠረ በታሪክ 6ኛው ተጫዋች ሲሆን፣ ባለፉት 50 ዓመታት ደግሞ ከእንግሊዙ ሃሪ ኬን (2018) ቀጥሎ ሁለተኛው ተጫዋች ሆኗል። የሃላንድ የቅርብ ጊዜ የብሔራዊ ቡድን አቋምም እጅግ አስደንጋጭ ነው። በተከታታይ 12 የብሔራዊ ቡድን የውድድር ጨዋታዎች ላይ ግብ ያስቆጠረ ሲሆን፣ ባለፉት 6 ጨዋታዎች ብቻ 16 ግቦችን መረብ ላይ አሳርፏል። አጠቃላይ የብሔራዊ ቡድን ግቦችን ስንመለከት በ100 የብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች 60 ግቦችን ካስቆጠረው ኤምባፔ ጋር ሲነጻጸር፣ ሃላንድ በ52 ጨዋታዎች ብቻ 59 ግቦችን በማስቆጠር (ከኤምባፔ በ48 ጨዋታዎች አንሶ) አንድ ግብ ብቻ ዝቅ ብሎ ይገኛል።

የሁለቱን ኮከቦች አጠቃላይ እንቅስቃሴ ስናነጻጽር በዚህ የውድድር ዘመን በክለብ ደረጃ ኤምባፔ ኳስ በመንካት፣ እድል በመፍጠር እና ሙከራ በማድረግ ከሃላንድ ይበልጣል። ምንም እንኳን ሃላንድ በማንችስተር ሲቲ የተሻለ አሲስት ቢኖረውም፣ በዚህ የዓለም ዋንጫ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ኤምባፔ 14 ስኬታማ ኳስ የማታለል እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ፣ ሃላንድ ያደረገው አንድ ብቻ ነው። ነገር ግን ኳስን ወደ ግብ በመቀየር ሃላንድ ትልቅ የበላይነት አለው። ባለፉት አራት የክለብ የውድድር ዘመናት 23.43% ሙከራዎቹን ወደ ግብ ሲቀይር፣ ኤምባፔ ግን 18.24% አሳክቷል። የመከላከል አስተዋጽኦን በተመለከተ ኤምባፔ ወደ ኋላ ተመልሶ በመከላከል ረገድ ከሃላንድ እጅግ ያንሳል። ለሪያል ማድሪድ በዚህ ዓመት ሲጫወት ከ900 ደቂቃ በላይ ከተጫወቱ 1,483 የአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች ተጫዋቾች ውስጥ በመከላከል አስተዋጽኦ 1,481ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

የሁለቱ ኮከቦች ለሀገራቸው ያላቸው ፋይዳ በቅርብ ጊዜ የግብ ተሳትፎአቸው በግልጽ ይታያል። ከነሐሴ 2022 ጀምሮ ኤምባፔ በ44% የፈረንሳይ ግቦች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ በማድረግ 33 ግቦችን እና 17 አሲስቶችን ሲያበረክት፣ ሃላንድ ደግሞ በ43.9% የኖርዌይ ግቦች ላይ ተሳትፎ በማድረግ 39 ግቦችን እና 4 አሲስቶችን አድርጓል።

ፈረንሳይ ዋንጫውን ለማንሳት ከፍተኛ ግምት ከተሰጣቸው ሀገራት ቀዳሚዋ ናት፤ ሃላንድ ራሱ ሳይቀር ፈረንሳይ ዐርቡን ጨዋታ አሸንፋ ዋንጫውን ልትወስድ እንደምትችል በቅርቡ ተናግሯል። ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት በዓለማችን እጅግ አደገኛው የግብ ክልል አጥቂ የሆነውን ሃላንድን የያዘችው ኖርዌይ፣ በፈረንሳይ ላይ ያልታሰበ አደጋ ልትፈጥር እንደምትችል መገመት አያዳግትም። ሃላንድን ይዞ የኖርዌይን ጉዞ ይሄን ያህል ነው ብሎ መገደብ ሞኝነት ነው!

4 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.