Logo
FBC
ሻምፒዮኑ አርሰናል ከሻምፒዮንሺፑ አሸናፊ ኮቬንትሪ ሲቲ …

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ2026/27 የውድድር ዘመን የጨዋታ መርሐ ግብር በትናንትናው ዕለት ይፋ መደረጉ ይታወቃል፡፡

በዚህም የወቅቱ የሊጉ ሻምፒዮን አርሰናል ከሻምፒዮንሺፑ አሸናፊ ኮቬንትሪ ሲቲ ጋር በሜዳው ኢምሬትስ የሊጉን የመክፈቻ ጨዋታ ያደርጋል፡፡

ኮቬንትሪ ሲቲ ለመጨረሻ ጊዜ በአንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የተሳተፈው በ2000/01 የውድድር ዓመት እንደነበር ይታወሳል፡፡

በዚያ የውድድር ዓመት በሊጉ ካደረጋቸው 38 ጨዋታዎች 34 ነጥብ በመሰብሰብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወደ ሻምፒዮንሺፕ ለመውረድ ተገዷል፡፡

ክለቡ በአሰልጣኝ ፍራንክ ላምፓርድ እየተመራ ከዓመታት በኋላ በአስደናቂ ብቃት
ለ2026/27 የውድድር ዘመን ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ማደጉ ይታወሳል፡፡

የ2026/27 የውድድር ዓመት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የመክፈቻ ጨዋታ የፕሪሚየር ሊጉና የሻምፒዮንሺፑ አሸናፊ ቡድኖች በሚያደርጉት ጨዋታ ይጀምራል፡፡

አርሰናል በ3ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ ግብር በሜዳው ቼልሲን የሚያስተናግድበት የለንደን ደርቢ ጨዋታ ተጠባቂ ነው፡፡

አርሰናል በ9ኛ ሳምንት ከሊቨርፑል፣ በ12ኛ ሳምንት ከማንቼስተር ሲቲ፣ በ14ኛ ሳምንት ከቶተንሃም ሆትስፐር እንዲሁም በ16ኛ ሳምንት ከማንቼስተር ዩናይትድ ጋር ይገናኛል፡፡

ከአሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ጋር በመለያየት አሰልጣኝ ኢንዞ ማሬስካን በኃላፊነት የሾመው ማንችስተር ሲቲ በሜዳው ከቦርንማውዝ ጋር የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታውን የሚያደርግ ይሆናል፡፡

አሰልጣኝ ኢንዞ ማሬስካ በማንቼስተር ሲቲ ቤት ከዚህ ቀደም በምክትል አሰልጣኝነት የሰሩ ሲሆን፥ በአዲሱ የውድድር ዓመት በዋና አሰልጣኝነት የሚያደርጉት ጉዞ ይጠበቃል፡፡

ማንቼስተር ሲቲ ከማንቼስተር ዩናይትድ ጋር በ4ኛ ሳምንት እንዲሁም ከሊቨርፑል ጋር በ6ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ይገናኛል።

በአሰልጣኝ ማይክል ካሪክ የሚመራው ማንቼስተር ዩናይትድ በበኩሉ ከአዲስ አዳጊው ሃል ሲቲ ጋር በመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታው ይገናኛል፡፡

ማንቼስተር ዩናይትድ ከአሰልጣኝ ማይክል ካሪክ ቅጥር በኋላ በመሻሻል የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ተሳትፎ ቦታን በማግኘት የውድድር ዓመቱን ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡

ከ4ኛ ሳምንት የማንቼስተር ደርቢ ጨዋታ በኋላ በ9ኛ ሳምንት ከቼልሲ፣ በ11ኛ ሳምንት ከሊቨርፑል እንዲሁም በ16ኛ ሳምንት ደግሞ ከወቅቱ የሊጉ ሻምፒዮን አርሰናል ጋር ይገናኛል፡፡

አንዶኒ ኢራዮላን በኋላፊነት የሾመው ሊቨርፑል ከኒውካስል ዩናይትድ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታውን ያደርጋል፡፡

ሊቨርፑል በ6ኛ ሳምንት ከማንቼስተር ሲቲ፣ በ9ኛ ሳምንት ከአርሰናል፣ በ11ኛ ሳምንት ከማንቼስተር ዩናይትድ እንዲሁም በ12ኛ ሳምንት ደግሞ በመርሲሳይድ ደርቢ ከኤቨርተን ይፋለማል፡፡

ከአውሮፓ ውድድሮች ውጪ ሆኖ የውድድር ዓመቱን ያጠናቀቀው ቼልሲ በመጀመሪያ ሳምንት ከፉልሃም ጨዋታውን ያደርጋል፡፡

ቼልሲ አዲሱን የውድድር ዓመት በአሰልጣኝ ዣቢ አሎንሶ እየተመራ የሚጀምር ይሆናል፡፡

በመርሐ ግብሩ መሰረት አዲሱ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር ዘመን ነሐሴ 15 ቀን 2018 ዓ.ም የሚጀመር ይሆናል፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ

4 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.