Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) ሜክሲኮ የአለም ዋንጫን ደህንነት ለመጠበቅ በስታዲየሞች የውሻ ሮቦቶችን አሰማርታለች፡፡ በሜክሲኮ እየተካሄደ ባለው የፊፋ አለም ዋንጫ ውድድሮች ላይ በስታዲየሞች የደህንነት ጥበቃ እያደረጉ የሚገኙት የውሻ ሮቦቶች የበርካቶችን ቀልብ ስበዋል፡፡

እነዚህ ሮቦቶች ኤችዲ ካሜራ የተገጠመላቸውና በርካታ ህዝብ ባለበት ቦታ ላይ ቅኝት እንዲያደርጉ በሚል ዲዛይን የተደረጉ ናቸው፡፡ ‹‹ኬ6 ኤክስ›› የሚል መጠሪያ ያላቸው እነዚህ ሮቦቶች በጨለማም ማየት የሚችሉ ሲሆኑ ያዩትን ነገር ሁሉ በቀጥታ ለማእከላዊ ትእዛዝ ማእከል ያስተላልፋሉ፡፡ እንዲሁም በውስጣቸው በተገጠመው ስፒከር አማካኝነት ትእዛዝ ይሰጣሉ፡፡

ማለትም ለሰዎች ‹‹ወደኋላ ተመለስ፣ ውጣ ወይንም የያዝከውን ጣል›› የሚል መልእክት የሚናገሩ ናቸው፡፡ ከመጠናቸው አኳያ ፖሊሶች መድረስ ወደማይችሉባቸው ቦታዎች በመሄድም ፍተሻዎችን ያከናውናሉ፡፡ ከዚህ ቀደም በኮንካካፍ ሻምፒዮን ውድድር ወቅት ተሰማርተው ብቃታቸውን ያስመሰከሩም ናቸው፡፡ ለእነዚህ ሮቦቶች መከሰት ዋነኛ ምክንያት የሆነው ባለፈው አመት በሞንቴሪ አካባቢ በቅኝት ላይ የነበሩ 2 ፖሊሶች መገደል ነው፡፡ የከተማው ከንቲባ ሄክቶር ጋርሺያ በስራ ላይ ያሉ ፖሊሶች የሚደርስባቸውን ከአደጋ ለመቀነስ በቴክኖሎጂ እንዲታገዙ የሚል መመሪያ ያወጣሉ፡፡

ይህንን መመሪያ ተከትሎ አራት እግር ያላቸው ሮቦቶች በከተማው ውስጥ ሊሰማሩ ችለዋል፡፡ እነዚህ 4 ሮቦቶች ከተማውን በአጠቃላይ 145,000 ዶላር ያስወጡት ቢሆንም አሁን ግን ያለምንም ጦር መሳሪያና የፖሊሶች አካላዊ ጉዳት አደገኛ ወደሆነ ቦታ ጭምር እየገቡ ጥበቃ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ እንደዚህ አይነት የጥበቃ ስርአቶች በሲንጋፖር፣ ጣሊያን፣ ኔዘርላንድና ሌሎችም አገራት ስራ ላይ መዋላቸው የሚታወቅ ነው፡፡ የሞንቴሪ ከተማ አስተዳደር ለአለም ዋንጫ ውድድሮች ደህንነት እነዚህን የውሻ ሮቦቶች ብቻ አላሰማራም፡፡ ሁለት ብላክ ሀውክ ሄሊኮፕተሮች፣ 90 ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች፣ ድሮኖችና የፀረ ድሮን ቴክኖሎጂ 24 ሰአት ሙሉ ከተማውን የሚቃኙና የሚጠብቁ ሲሆን እነዚህን የሚቆጣጠር አንድ ማእከላዊ ማእከልም ተቋቁሟል፡፡

4 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.