Logo
FBC
ለኢትዮጵያ አዲስ የፖለቲካ ባህል ያመጣው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የፖለቲካ ፓርቲዎች 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ልምምድ ታሪክ የሰላማዊ ፖለቲካ ውድድር እና የሕዝብ ተሳትፎ መጠናከርን ያሳየ ነው አሉ።

በብልፅግና ፓርቲ ኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ሞገስ ኤዴዔ እንዳሉት÷ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያን የምርጫ ታሪክና ሂደት በመቀየር በሀገሪቱ አስተማማኝና ዘመናዊ የዴሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት የሚያስችል አዲስ የፖለቲካ ባህል ተመዝግቧል።

ኋላ ቀርና በኃይል የመጠቀም የፖለቲካ ፉክክር ሥርዓት በመቀየር በትብብር እና በፖለቲካዊ ውድድር መርህ ላይ የተመሰረተ አዲስ አሰራር በተግባር መታየቱንም አስረድተዋል።

ሰኞ ምርጫ አከናውነን ማክሰኞ ወደ ሥራ እንገባለን ያልነውን አሳክተናል ያሉት ኃላፊው÷ ምርጫው ኢትዮጵያ አሸናፊ የሆነችበት የታሪክ ምዕራፍ ሆኖ ማለፉን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ በሰላማዊ መንገድ ድምፅ የመስጠት ሂደትና ያሳየው ትዕግስት በዓለም አቀፍና በውጭ ታዛቢዎች ዘንድ አድናቆትና ምስክርነት ተሰጥቶታልም ነው ያሉት።

የኢዜማ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት ታሪኩ ድንበሩ በበኩላቸው÷ ባለፉት ስድስት ምርጫዎች ይስተዋሉ የነበሩ የፖለቲካ ምልክቶች፣ የሚዲያ አጠቃቀም እና የመንግሥት ተቋማት ምላሽ ሰጪነት ተግዳሮቶች በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ አለመታየታቸውን አመልክተዋል።

እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቶች በመወያየት የተፈጠሩ ችግሮች መፍትሄ ያገኙበት ልዩ ሂደት የነበረበትና የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴዎች በቦታው ተገኝተው ፈጣን ምላሽ የሰጡበት ሁኔታ መኖሩን አንስተዋል።

በቀጣይም በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራትና የምርጫው ውጤት ሲገለጽ ውጤቱን በጸጋ በመቀበል ለሀገር ግንባታ በትብብር መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በሶስና አለማየሁ

4 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.