Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) በአለም ዋንጫ የሚሳተፉት የኢራን ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች የተሰጣቸው የአሜሪካ ቪዛ የ1 ቀን መሆኑ ተሰማ፡፡ በ2026 አለም ዋንጫ የሚሳተፈው የኢራን ብሄራዊ ቡድን የአሜሪካ መግቢያ ቪዛ እንደተሰጠው መገለፁ ይታወሳል፡፡ ይህንን ተከትሎ የብሄራዊ ቡድኑን አባላት የጫነው አውሮፕላን ዛሬ በሜክሲኮ ድንበር የሚገኘው ቲጁአና ከተማ አርፏል፡፡ አውሮፕላኑ ከቱርክ ተነስቶ ስፔን ጥቂት ቆይታ ካደረገ በኋላ እዚህች ከተማ ያረፈው በውድድሩ ወቅት ዋና ካምፑን እዚያው ለማድረግ በማቀድ ነው፡፡

በሜክሲኮ፣ አሜሪካና ካናዳ የጋራ አዘጋጅነት በሚከናወነው የዘንድሮው አለም ዋንጫ የኢራን ቡድን ሁሉንም የምድብ ማጣሪያ ግጥሚያዎቹን በአሜሪካ እንደሚያደርግ ይታወቃል፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ ጨዋታዎቹ በካናዳ ወይንም በሜክሲኮ እንዲሆኑለት ጥያቄ ቢያቀርብም በፊፋ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ከቤልጂየምና ከኒውዚላንድ ጋር በሎስ አንጀለስ እንዲሁም ከግብፅ ጋር በሲያትል ጨዋታውን የሚያካሂድ ይሆናል፡፡ ነገር ግን በሜክሲኮ የሚገኙት የኢራን አምባሳደር ዛሬ እንደገለፁት ለብሄራዊ ቡድኑ አባላት የተሰጠው ቪዛ ‹‹ገብቶ የመውጣት›› የአንድ ቀን መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

አምባሳደሩ እንደሚሉት ተጨዋቾቹ በግጥሚያቸው እለት ከሜክሲኮዋ ቲጁአና ከተማ ተነስተው ወደአሜሪካ ስታዲየም የመጓዝ ቪዛ አላቸው፡፡ ይህ ቪዛ ግን ልክ የጨዋታው መጠናቀቅን የሚያበስረው ፊሽካ ሲሰማ የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡ በመሆኑም በጨዋታ እለት ተነስተው ወደአሜሪካ በመጓዝ ተመልሰው ወደሜክሲኮ ለመጓዝ እንደሚገደዱ አስታውቀዋል፡፡ ይህ መግለጫቸው ከዚህ ቀደም የኢራን እግርኳስ ፌዴሬሽን ቃል አቀባይ ከተናገሩት ጋር የሚቃረን ነው፡፡ ቃል አቀባዩ በንግግራቸው ተጨዋቾቹ በመጀመሪያው ግጥሚያ ከአንድ ቀን ቀደም ብለው አሜሪካ እንደሚገቡና በተከታይ ባሉት ሁለት ግጥሚያዎች ግን እለት 2 ቀን ቀደም ብለው ለመግባት የሚስችል ቪዛ እንደተሰጣቸው ተናግረው ነበር፡፡ ይ

ህ በእንዲህ እንዳለ የኢራን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንቱ ማህዲ ታጅ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ለብሄራዊ ቡድኑ ተጨዋቾች የተጠቀሰው ቪዛ ቢሰጥም 15 ለሚሆኑ የቡድኑ አባላት ግን ቪዛ መከልከሉን ገልፀዋል፡፡ ይህም አግባብ አለመሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በተያያዘ አሜሪካና ኢራን ከየምድባቸው ሁለተኛ ሆነው የሚያጠናቅቁ ከሆነ በቀጣይ እርስ በእርሳቸው እንደሚጋጠሙ የወጣው መርሀ ግብር ያሳያል፡፡ በመርሀ ግብሩ መሰረት ሁለቱም ከምድባቸው 2ተኛ ሆነው ካጠናቀቁ ግጥሚያቸው ጁላይ 3 ቀን በቴክሳስ አርሊንግተን ይሆናል፡፡

4 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.