Logo
FBC
ሰላም! ደህና አደራችሁ ውድ ኢትዮጵያውያን?

በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ ድምጹን ላሻው በመስጠት ሀገር ወዳድነቱን እና የዴሞክራሲ ልምምድ ፍላጎቱን በተግባር አሳይቷል።

ድምጽ የመስጠቱ ሂደት ማለዳ 12:00 ጀምሮ ሲካሄድ የቆየ ቢሆንም ምሽት 12:00 ድረስ ባለመጠናቀቁ ምርጫ ቦርድ መራጩ የመምረጥ መብቱን እንዲጠቀም እስከ ለሊት 6:00 አራዝሞለት መራጩም እድሉን ተጠቅሟል።

በዚህ ምርጫ ህዝቡ እኔ አውቅልሃለሁ ለሚለው ሁሉ፣ በሰላም ወጥቶ በመምረጥ ባሳየው ቁርጠኝነት አይ እኔ ለራሴ አውቃለሁ፣ ሀገሬን በሰላማዊ መንገድ ለትውልድ አሻግራለሁ ያለበት ነው።

ማሳያውም የምርጫ ውሎው ነው።

እርጅና፣ አካል ጉዳት፣ ህመም፣ ኅዘን፣ ወሊድ፣ ሰርግ፣ ብርድ፣ ዝናብ፣ ፀሐይ፣ ጭለማ አልበገረውም።

ድምጹን ይወክለኛል ላለው በነፃነት ያለማንም ጫና ሰጥቷል።

በየምርጫ ጣቢያው የነበረውን ኢትዮጵያዊ ጨዋነት የአፍሪካ ሕብረት፣ የኢጋድ እና የሀገር ውስጥ የምርጫ ታዛቢዎች መስክረዋል።

በዚህ ምርጫ የተሳተፈው የመራጭ ቁጥር እና የመራጩ ጨዋነት ሲታይ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንጂ ጩኸትና የጠብመንጃ ማስፈራሪያ አያስፈልገኝም ያለበት ነው።

እናም ከዚህ በኋላ በኢትዮጵያ ምድር ጠብመንጃ እያወዛወዙ በኃይል ካልገዛሁህ ለሚሉት ሁሉ መሻታቸው ጊዜ ያለፈበት ተረት ተረት መሆኑን በተጨባጭ በድምጹ ወስኗል።

የሚበጀውም የህዝቡን የካርድ ምርጫ መጠበቅና ውሳኔውን መቀበል ብቻ ነው።

ህዝቡ አንዴ ወስኗል። ኢትዮጵያ የፍላጎቷን መርጣለች፤ ለውጤቱ ደግሞ ምርጫ ቦርድን ብቻ በትእግስት መጠበቅ ነው።

እኛ ኢትዮጵያውያንን በቅጡ የማያውቁ አካላት ሊለዩን፣ ሊበትኑን ብዙ ጊዜ ሞክረዋል። ከባእዳን በተጨማሪም የውስጥ ባንዳዎች ብዙ ጥረዋል።

ነገር ግን ለልዩነት የማንመች እና እርስ በራስ የተሰናሰልን ሀገራችንን የምንወድ ህዝቦች በመሆናችን ዛሬ ደርሰናል።

ትናንት ለሚወክለን ካርዳችንን በነጻነት ሰጥተናል።

በዚህ ዙርም ሊያውኩን ሞከረዋል፤ ነገር ግን አልሆነላቸውም፤ እኛ የዴሞክራሲ ልምምድን መርጠናል።

እነሱ ገና የድንጋይ ዘመን ላይ ናቸው። ወጋችንም አይገጥምም።

እኛ የጀግኖቹ የእናት አባቶቻችን ልጆች ነን።

ቀደምት እናት አባቶቻችን ከግል ፍላጎታቸው ይልቅ ለሀገራቸው ቅድሚያ በመስጠት የላብ፣ የደም፣ የአጥንት እና የህይወት መስዋእትነት ከፍለው ሀገር አውርሰውናል።

የአሁኑ ትውልድም ሀገሩን በሰላምና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለቀጣይ ትውልድ ለማሻገር በካርዱ ወስኗል።

በካርዳችን የሚሻንን መርጠናል። ማንም ቢያሸንፍ ሀገር ከፖለቲካ እና ከሁኔታዎች ሁሉ በላይ ናት።

አብሮነታችን ውበታችን ነው። በእናት አባቶቻችን ሀገር ወዳድነት ኢትዮጵያን ወርሰናል። እኛም በድምጻችን ሀገር ለማሻገር ተልመናል። ጉዟችን ወደ ሰላማዊው ዴሞክራሲ ብቻ ነው።

ኢትዮጵያ መርጣለች! ውሳኔዋንም እንቀበላለን!

2 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.