Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ከሶማሌላንድ ጋር ያለውን ግንኙነት እና ትብብር ማሻሻል በሚችልባቸው መስኮች ዙሪያ የተዘጋጀ ዝርዝር ሪፖርት ለኮንግረስ ቀረበ። የ2026 የብሔራዊ ደህንነት እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የበጀት አዋጅን መሠረት አድርጎ የወጣው ይህ ሪፖርት፣ አሜሪካ የሶማሊያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት (ሶማሌላንድን ጨምሮ) እንደምትቀበል በድጋሚ ያረጋገጠ ሲሆን፣ በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ ከሶማሌላንድ ባለስልጣናት ጋር አዎንታዊ እና ገንቢ ግንኙነቷን እንደምትቀጥል አስታውቋል። ሪፖርቱ ግንኙነቱ ሊሻሻልባቸው የሚችሉ ሦስት ዋና ዋና መስኮችን በዝርዝር አስቀምጧል፡-

በአፍሪካ ቀንድ ያለው የጸጥታ ሁኔታ አሁንም ውስብስብ መሆኑን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ የጽንፈኛ ኃይሎች ስጋት እና የቀጠናው አለመግባባቶች አሳሳቢ እንደሆኑ ገልጿል። ይሁን እንጂ ሶማሌላንድ ከየመን እና ከባቢ ኤል-ማንደብ ባህረ ሰላጤ አቅራቢያ ያላት ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ፣ ከቀይ ባህር እስከ ህንድ ውቅያኖስ ያለውን የንግድ እና ወታደራዊ የባህር ላይ ጉዞ ነፃነት ለማረጋገጥ ወሳኝ አጋር ያደርጋታል። በተጨማሪም የሁቲ ታጣቂዎች እና የአልቃይዳ ትልቁ ክንፍ ከሆነው አል-ሸባብ ጋር ያላቸውን ትስስር ለመቆጣጠር እና የሽብርተኞችን እንቅስቃሴ ለመግታት የሶማሌላንድ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ አመቺ መሆኑ ተገልጿል። ለዚህም ሲባል የአሜሪካ የአፍሪካ ዕዝ (AFRICOM) ከሶማሌላንድ ባለስልጣናት ጋር መደበኛ ግንኙነት እያደረገ መሆኑ ታውቋል።

በሞቃዲሾ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በጸጥታ፣ በሰብአዊ እርዳታ እና በኢኮኖሚ ጉዳዮች ዙሪያ ለመምከር ወደ ሶማሌላንድ መደበኛ ጉብኝቶችን እንደሚያደርግ ሪፖርቱ ጠቅሷል። ሆኖም የአሜሪካ መንግሥት ሠራተኞች ወደ ስፍራው የሚያደርጉት ጉዞ ልክ እንደሌላው የሶማሊያ ክፍል ጥብቅ የጸጥታ መስፈርቶችን የሚጠይቅ ነው። በመሆኑም የንግድ ያልሆኑ አውሮፕላኖችን እና ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ የጸጥታ ጥበቃዎችን መጠቀም ግድ ይላል። ይህንን ሒደት ለማቀላጠፍ ኤምባሲው ከአፍሪካ ዕዝ ወታደራዊ ሀብቶች ጋር በቅርበት በማስተባበር እየሰራ ይገኛል።

የሶማሌላንድ ባለስልጣናት አሜሪካ በማዕድን፣ በመሰረተ ልማት፣ በንግድ እና በኢኮኖሚ ዕድገት ዘርፎች ኢንቨስት እንድታደርግ ሰፊ ማበረታቻ እያደረጉ መሆኑን ሪፖርቱ አስፍሯል። የሶማሌላንድ ወደቦች በቀጠናው ላሉ ሌሎች መጨናነቅ ለሚታይባቸው ወደቦች እንደ አማራጭ ሊያገለግሉ እንደሚችሉ የተገለጸ ሲሆን፣ እየተገነባ ያለው የበርበራ አውሮፕላን ማረፊያ እና ወደብ ለሶማሌላንድም ሆነ የባህር በር ለሌላት ኢትዮጵያ የንግድ እና የትራንስፖርት ማዕከል እየሆነ መምጣቱ፣ ለአሜሪካ የኢንቨስትመንት እና የንግድ ዕድሎችን ሊፈጥር እንደሚችል ተገምቷል።

ነገር ግን የቀጠናው የጸጥታ ስጋት፣ በሶማሌላንድ ፖለቲካዊ ቁመና ላይ ያለው አለመግባባት እና ባለስልጣናቱ ከሶማሊያ ብሔራዊ መንግሥት ጋር ለመተባበር ፈቃደኛ አለመሆናቸው፣ በአሜሪካ የኢንቨስትመንት፣ የባንክ እና የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ ከባድ ተግዳሮት እንደፈጠረ ሪፖርቱ አብራርቷል።

4 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.