Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) ዛሬ በሚኒሶታ በተካሄደው የአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር አምባሳደር ብናልፍ ስብሰባ ላይ እነዚህን 4 ጥያቄዎች ለማቅረብ ፈልጌ ዕድል አልተሰጠኝም። አዘጋጆቹን ስጠይቅ ብዙ ጥያቄ አይፈቀድም ቀድሞ የተዘጋጁ ጥያቄዎች አሉ ብለውኛል። ግን እጄን አውጥቼ ዕድሉ ባይሰጠኝም ጥያቄዎቼን ሕዝብ እንዲያውቅልኝ ሁሌም ለምተማመንበት ዘ-ሐበሻ ልኬያለሁ። ለነገሩ አምባሳደሩ ለተጠየቁት ጥያቄ ለአብዛኛው መልስ ሳይሰጡ ነው የወጡትና እኔም ዕድሉን ባገኝ ጥያቄዬን ሰምተው እንደማይመልሱት ብገምትም፣ ሕዝብ ግን ሰፊ ተደራሽነት ባለው ዘ-ሐበሻ ጥያቄዬን ይስማ።

1ኛ. አምባሳደር ብናልፍ ፣ እርስዎ ወደዚህ ኃላፊነት ከመምጣትዎ በፊት ለሦስት ዓመታት የሀገሪቱ 'የሰላም ሚኒስትር' ነበሩ። ነገር ግን በእርስዎ የሥልጣን ዘመንም ሆነ አሁን በተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች ደም መፋሰሱ አልቆመም፤ ንጹሃን በድሮን እና በከባድ መሣሪያ እየተገደሉ ነው። የሰላም ሚኒስትር ሆነው ማምጣት ያልቻሉትን ሰላም፣ አሁን አምባሳደር ሆነው በምን አዲስ ስትራቴጂ ሊያመጡት አስበዋል? ወይስ አሁንም መፍትሔው ኃይል ብቻ ነው ብላችሁ ታምናላችሁ?

2ኛ. መንግሥት በውጭ ሀገር መድረኮች ላይ ስለ ዴሞክራሲ እና ብሔራዊ ምክክር በሰፊው ይናገራል። በተግባር ግን በርካታ ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና የመብት ተሟጋቾች ያለምንም ክስ በእስር ቤት ይማቅቃሉ። እርስዎ የኢትዮጵያን መንግሥት ወክለው በአሜሪካ ሲሟገቱ፣ ይህንን በዜጎች ላይ የሚደርስ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና የፖለቲካ አፈና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ (እና ለዲያስፖራው) ምን ዓይነት የሞራል ማመኻኛ ሊያቀርቡለት ይችላሉ?

3ኛ. በቅርቡ ከፕሬዚዳንት ትራምፕ እና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጋር ተገናኝታችኋል። የአሜሪካ መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት እንዲያጠናክር (ለምሳሌ የ AGOA ዕድል እንዲመለስ) ጥረት እያደረጋችሁ እንደሆነ ይነገራል። ነገር ግን አሜሪካ የሰብዓዊ መብት መከበርን እንደ ቅድመ-ሁኔታ ታስቀምጣለች። የገዛ ዜጎቹን በሰላም ማስተዳደር ያቃተው መንግሥት፣ እንዴት የውጭ ሀገራትን አመኔታ ሊያገኝ ይችላል? በተጨማሪም የተለየ ሃሳብ ያለውን ዲያስፖራ 'ጽንፈኛ' እያለ የሚያገል መንግሥት፣ ዛሬ በሚኒሶታ ከእኛ ጋር እንዴት እውነተኛ መተማመን ሊፈጥር ይችላል?

4ኛ. በአሁኑ ወቅት በሀገር ውስጥ ያለው የኑሮ ውድነት ሕዝቡን እያማረረው ነው፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች በጦርነት ተፈናቅለው የዕለት ደራሽ እርዳታ ይፈልጋሉ። ይህ እውነት ሆኖ ሳለ፣ መንግሥት ቢሊዮኖችን እያፈሰሰ ለሚገነባቸው የቤተ-መንግሥት እና የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች ቅድሚያ መስጠቱ ከሕዝቡ የህልውና ጥያቄ ጋር እንዴት ይጣጣማል?

አብዱራሂም መሐመድ ነኝ ከፍሪድሊ፣ ሚኒሶታ

20 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.