Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) ወልታ ጽድቅ ዘተዋሕዶ ዓለም አቀፍ የመነኮሳት ጉባኤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አባላትን "ለሥልጣን እና ለመንግሥት ባለሥልጣናት በማጎብደድ መንጋውን ለተኩላ አሳልፈው ሰጥተዋል" ሲል በጽኑ የሚወቅስ ባለ ስድስት ነጥብ ይፋዊ መግለጫ አወጣ። ማኅበሩ ግንቦት 4 ቀን 2018 ዓ.ም ባወጣው እና "የሚያሰማራቸውን በጎች ለሚያጠፉ እና ለሚበትኑ እረኞች ወዮላቸው" በሚለው የነቢዩ ኤርምያስ ቃል በጀመረው በዚህ መግለጫ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች አሁን ባለው የፈተና ጊዜ እያሳዩት ያለው ዝምታ ታሪካዊ እና መንፈሳዊ ተጠያቂነትን እንደሚያስከትልባቸው አሳስቧል።

ማኅበሩ በመግለጫው እንዳብራራው፣ ኦርቶዶክሳውያን በግፍ እየተገደሉ፣ ከቀያቸው እየተፈናቀሉ እና ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ፈተና ውስጥ ባለችበት በዚህ ወቅት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የህዝቡን ስቃይ እና ሰቆቃ ችላ ብለዋል። አባቶች ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ያላቸውን ግንኙነት ላለማበላሸት ሲሉ ብቻ እውነታውን መናገር መፍራታቸውን ጠቅሶ፣ "ከእግዚአብሔር ይልቅ ሰውን መፍራት" በሚል በብርቱ ኮንኗቸዋል። አያይዞም ሲኖዶሱ የሕዝብን እንባ ከማበስ ይልቅ ወቅታዊ ሁኔታን ያላገናዘቡ እና "ለባለሥልጣናት ማስታገሻ" የሚሆኑ መግለጫዎችን ማውጣቱን አጥብቆ ተችቷል።

የመነኮሳት ጉባኤው ለቅዱስ ሲኖዶሱ ካቀረባቸው ጥብቅ ማሳሰቢያዎች መካከል የኦርቶዶክሳውያን ደም መፍሰስ ጉዳይ ቀዳሚውን ስፍራ ይዟል። በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች (በተለይም በኦሮሚያ፣ በጅማ፣ በምዕራብ ሐረርጌ እና በሌሎችም አካባቢዎች) በምእመናን ላይ እየደረሰ ያለውን ሞት እና መፈናቀል አባቶች በግልጽ እንዲያወግዙ እና ዝምታቸውን እንዲሰብሩ ጠይቋል። አስመሳይ መግለጫዎችን ከማውጣት ይልቅ ለተገደሉት ጸሎተ ፍትሐት በማድረግ እና የተፈናቀሉትን በማጽናናት አባታዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስቧል።

በተጨማሪም የቤተ ክርስቲያኒቱ የገንዘብ እና የባንክ ሂሳብ ያለ ቤተ ክርስቲያኒቱ ፈቃድ በመንግሥት አካላት በግፍ መታገዱን እና መዘረፉን አስታውሶ፣ አባቶች ይህን ሕገ-ወጥ ድርጊት በዝምታ ማለፋቸው አሳዛኝ መሆኑን ገልጿል። ቤተ ክርስቲያን በማንም እየተደፈረች እና እየተሰደበች ባለችበት በዚህ ዘመን አባቶች የቤተ ክርስቲያን ጠበቃ መሆን ሲገባቸው፣ በተቃራኒው መንግሥትን ላለማስቀየም የሚያደርጉትን ጥረት በአስቸኳይ እንዲያቆሙ ሞግቷል።

መግለጫው ከሀገር ውስጥ አባቶች ባለፈ በውጭ ሀገር (ዲያስፖራ) በሚገኙ ሊቃነ ጳጳሳት ላይም ብርቱ ትችት ሰንዝሯል። እነዚህ አባቶች በውጭ ሀገር ሲሆኑ የምእመናንን ችግር እንደሚረዱ እና እንደሚቆረቆሩ መስለው እንደሚናገሩ፣ ነገር ግን ለቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ አዲስ አበባ ሲገቡ አቋማቸውን እንደሚቀይሩ እና እውነታውን ለሲኖዶሱ ከማቅረብ ይልቅ ተባባሪ እንደሚሆኑ ማኅበሩ አጋልጧል። ይህ ዓይነቱ ድርብ ማንነት ሊታረም እንደሚገባው እና አባቶች የትም ቦታ ቢሆኑ ለቤተ ክርስቲያን እና ለእውነት ብቻ እንዲቆሙ አሳስቧል።

ወልታ ጽድቅ ዓለም አቀፍ የመነኮሳት ጉባኤ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በንስሐ ተመልሰው የመንጋውን ድምጽ እንዲሰሙ፣ ያለበለዚያ ግን የእግዚአብሔር የፍርድ ሚዛን እንደማይምራቸው መንፈሳዊ ማስጠንቀቂያ በመስጠት መግለጫውን አጠናቋል።

20 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.