Logo
Zehabesha
በጠንካራ መርህ ላይ የተመሰረተ ህይወት ወይም ስነስርአት(Discipline)፦የስኬትና የማደግ ሁሉ መሠረት ነው ::

በጠንካራ መርህ ወይንም ስነስርአት የሰው ልጅ በህይወቱ ሊያሳድገውና ሊያዳብረው የሚገባ እጅግ ኃያል የሆነ መሣሪያ ነው። ተነሣሽነት ይመጣል ይሄዳል ነገር ግን ስነሥርዓት በክፉ ቀንም ቢሆን አንኳ ሰዎች የህይወት ጉዞአቸው ሳይቋረጥ ወደፊት እንዲቀጥል ያግዛል ።

እውነተኛው ስነሥርዓት ማለት መደረግ ያለበትን ነገር- ማድረግ በማንፈልግበት ሰአት እንኳ ቢሆን- ወጥና ቋሚ በሆነ መንገድ መከወን ማለት ነው። ከጊዜያዊ ምቾት ወይም የሚያዘናጉ ነገሮች ይልቅ በረዥም ጊዜ ግቦች ላይ ማተኮር ማለት ነው።

ጤናችንን ማሻሻል ፣ በየቀኑ የአካል ብቃት እንቅሰቃሴ መስራት ፣ ጤናማ አመጋገብ መከተል፣ ጭንቀትን ማስወገድ ፣ ቢዝነሳችንን ማሳደግ፣ ማህበራዊ ግንኙነታችንን መሻሻል ወይንም ከነዚህ የተለየ የግል ግቦቻችንን ማሳካት ሊሆን ይችላል፤ ስነሥርዓት ወይም ጠንካራ የህይወት መርህ እነዚህን ግቦች በማሳካት ሂደት ከፍተኛውን ሚና ይጫወታል።

ትንንሽ የምንላቸው የየቀን ልማዶች በወጥነት ከተደጋገሙ በጊዜ ሂደት ይህ ነው የማይባል ለውጥ ያመጣሉ። በጥዋት መነሣት፣ በአካል ንቁ ሆኖ መገኘት ፣ በቂ ውሀ መጠጣት፣ ማንበብ፣ መማር፣ ጎጂ ልማዶችን ማስወገድ እና የሰውነታችንን ቅርፅ መጠበቅ ሊሆን ይችላል። እነዚህ ሁሉ በተግባር የሚታዩ የስነሥርዓት ምሳሌዎች ናቸው።

ስነሥርዓት ወይም ጠንካራ የህይወት መርህ ፍፁማዊነት አይደለም። ሁሉም ሰው ፈተናና እንቅፋት ያጋጥመዋል ። ከሁሉም ወሳኙ ነገር ጉዞአችንን በወጥነት፣ በትዕግሥትና ራስን በገዛ መልኩ ወደፊት ማስቀጠል ነው።

በብዙ መልኩ ብናየው ስነሥርዓት ያለው ህይወት ማለት ራስን ስለማክበር ነው። በጥቅሉ ሰዎች ህይወታቸውን ለማሻሻል ፣ ጤናቸውን ለመከላከልና የተሻለ ነገን ለመፍጠር በየቀኑ የሚያደርጓቸው ውሳኔዎ ነፀብራቅ ነው ልንለው እንችላለን።

በዶክተር ሲራክ ኃይሉ-
የካይሮፕራክቲክ ሐኪም
ሚኒሶታ

5 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.