Logo
FBC
በተለዋዋጩ የዓለም ሁኔታ ውስጥ የጸናች ሀገር ለመገንባት …

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በተለዋዋጭና ውስብስብ ዓለም አቀፋዊ አውድ ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪ ለአንድ ሀገር የምርት ብቻ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ተደርጎ ይወሰዳል።

ከጥሬ እቃ አቅርቦት፣ ከገበያ ሰንሰለት፣ ከደንበኛ የተለጠጠ ፍላጎት እንዲሁም ከዓለም አቀፋዊ ወቅታዊ ክስተቶች አንጻር ዓለም ተለዋዋጭነት ይበዛበታል፡፡

ታዲያ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ጸንቶ መቆም፣ ችግሮችን ተቋቁሞ መቀጠል እና ሀገር በፈተና እንዳትናወጥ ማድረግ የሚችል አምራች ኢንዱስትሪ መገንባት ለአንድ ሀገር እጅግ አስፈላጊ እና የጥንካሬ መመዘኛም ነው።

ይህንን መሰረት በማድረግ መንግሥት የሀገር ውስጥ ምርታማነትን ለማሳደግ ከሚሰራባቸው ዘርፈ ብዙ ሥራዎች መካከል አንዱ አምራች ኢንዱስትሪ ነው።

ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግም “የኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ መተግበር ከጀመረ ውሎ አድሯል።

ንቅናቄው የኢንዱስትሪውን እንቅስቃሴ ከማፋጠን ባለፈ ኢትዮጵያ ወደ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለምታደርገውን ጉዞ እውን መሆን የጎላ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ኢንዱስትሪዎች ይገጥሟቸው የነበሩ ችግሮችን በመፍታት የማምረት አቅማቸው እንዲጎለብት ከማድረግ በተጨማሪ በርካታ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ አስችሏል።

ንቅናቄው መዋቅራዊ ማነቆዎችን በመፍታትና የአምራች ዘርፉን አቅም ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር ሀገራዊ ብልጽግናን በተግባር እያረጋገጠ ሲሆን፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተደረገ የተቀናጀ ጥረት፣ በዘርፉ የታየው ዕድገትና የተመዘገቡት ስኬቶች ለዚህ ማሳያ ናቸው።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) የ2018 በጀት ዓመት የ100 ቀናት ግምገማ እና የ9 ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት፤ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ከለውጡ ወዲህ ቁልፍ ውጤት ተገኝቶበታል።

ከጠቅላላ ሀገራዊ ምርት የዘርፎችን ድርሻ በተመለከተ የኢንዱስትሪው ዘርፍ በ2010 ዓ.ም 27 በመቶ ድርሻ የነበረው ሲሆን በ2017 ዓ.ም ወደ 30 በመቶ ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።

የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት፣ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ማስገኘት፣ የሥራ እድል መፍጠር እና ሌሎችም ዐበይት ዓላማዎች የሰነቀ ሲሆን ኢንቨስትመንትን በመሳብ እና ገበያን በማረጋጋት ረገድም ሚናው ከፍተኛ ነው።

በብርሃኑ አበራ

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.