Logo
SeledaPost
"ጦርነቱ በማንኛውም ሰአት ሊፈነዳ ይችላል"

የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጦርነት ምናልባትም በሰአታት ውስጥ ጭምር ሊፈነዳ ይችላል ሲል አለምአቀፍ ተቋሙ ከባድ ማስጠንቀቂያ አወጣ፡፡

ዋነኛ ትኩረቱን በሠላም እና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ አድርጎ የሚሰራው International Crisis Group በዛሬው ዕለት ኢትዮጵያን እና ኤርትራን እንደዚሁም በትግራይ ክልል ያለውን አሳሳቢ ሁኔታ አስመልክቶ የጥናት ሪፖርት ይፋ አድርጓል።
ዓለም አቀፉ ተቋም ባወጣው አዲስ የጥናት ሪፖርት ላይ እንደተለመላከተው በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል እየተባባሰ የመጣው ውጥረት እንደዚሁም በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል መልሶ እያገረሸ ያለው የግጭት አዝማሚያ ወደ ጦርነት ሊቀየር ከጫፍ ላይ ደርሷል ሲል አሳስቧል።

በዐቢይ አህመድ እና በኢሳያስ መንግሥትታት እንደዚሁም በህወሓት መካከል ያለው የተወሳሰበ እና በውጥረት የታጀበውን ግንኙነት “በአፍሪካ ቀንድ በማንኛውም ቅፅበት ሊፈነዳ የሚችል የባሩድ በርሜል” ሲል International Crisis Group የሁኔታውን አሳሳቢነት በሪፖርቱ ገልጾታል።   ሪፖርቱ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2018 ዓመተ-ምህረት በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ተፈርሞ የነበረው “የአዲስ አበባ-አሥመራ-ባሕር ዳር” ወታደራዊ ጥምረት ሙሉ በሙሉ ፈርሶ፣ አሁን ላይ ሁለቱ ሀገራት እርስ በእርስ ወደ መጠላላትና ወደ ጦርነት እየተንደረደሩ ነው ሲል ያትታል።

ተቋሙ ባወጣው መግለጫ የተለያዩ ምክንያቶች ጦርነቱን ሊያፈነዱት እንደሚችሉ ያስጠነቀቀ ሲሆን፤ ወደ ጦርነት ዘው ብሎ ለመግባት ቀላል ቢሆንም ጦርነቱን ለማቆም ግን በጣም ከባድ ይሆናል ብሏል። የአፍሪካ የፕሮግራም ዳይሬክተር የሆኑት ሙሪታ ሙቲጋ “ኢትዮጵያን፣ ኤርትራን እና ትግራይ ክልልን የሚያፋልም አዲስ ጦርነት መቋቋም የማይቻል ዋጋ ያለው ነው። አደጋው ሦስቱንም ወገኖች ለአሁኑ እንዲታቀቡ ያደረጋቸው ይመስላል። ሆኖም እንዳያገረሽ ከዚህ በላይ መደረግ አለበት” ብለዋል።

የድርጅቱ ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ማግነስ ታይለር ከትግራይ ጦርነት መቋጨት በኋላ በዋናነት ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የባህር በር የማግኘት ፍላጎት ምክንያት የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግንኙነት መሻከሩን አንስተዋል። ኤርትራ ይህ ፍላጎት “ወረራን ሊያካትት ይችላል” የሚል ስጋት እንዳላትም ጠቁመዋል። ምክትል ዳይሬከተሩ አዲስ አበባ ህውሓት ከኤርትራ ጋር ስውር ትብብር መስርቷል ስትል እንደምትከስ ተናግረዋል።

የክራይስስ ግሩፕ መግለጫ በቅርቡ በፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ ኃይሎች የድሮን ጥቃትን ያካተተው ግጭት ኤርትራንም በመሳብ ወደ ሰፊ ጦርነት ሊቀየር እንደሚችል ያሳያል ብሏል። ተቋሙ አክሎም በሰሜን ኢትዮጵያ አዲስ የሚቀሰቀስ ግጭት በሱዳን ካለው ግጭት ጋር ተደርቦ ኃያላን የውጭ ተዋንያንን እንደሚስብ እና ተለዋዋጭ የሆነውን የቀይ ባህር ቀጣናን እንደሚያውክ አስጠንቅቋል።

ክራይስስ ግሩፕ ተፅዕኖ ፈጣሪ የአፍሪካ አገራት እና ዓለም አቀፍ አጋራት የዲፕሎማሲያዊ ሥራቸውን እንዲጨምሩ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህወሓትን እንዲያሸማግሉ ጠይቋል። አክሎም የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ፍላጎትን እና የኤርትራን ሉዓላዊነቷ ላይ ጥቃት የመሰንዘር ስጋትን ጨምሮ በሁለቱም በኩል ያሉ ወገኖች ቁርሾዎችን እንዲፈቱ ጥሪ አቅርቧል።

seledadotio
seledadotio
8 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.