Logo
FIDEL POST NEWS
ፉድ ዞን ፈረሰ፡ የቦሌው የኮሪደር ልማትና የመዲናዋ አዲስ ገጽታ

​በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወነ ባለው ሰፊ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ሳቢያ፣ በቦሌ መድኃኒዓለምና በአትላስ መካከል የሚገኘውና በበርካታ ወጣቶች ዘንድ ተወዳጅ የነበረው "ፉድ ዞን" (Food Zone) ሙሉ በሙሉ ፈርሷል

ይህ በክፍት አየር ላይ በሚሰጣቸው የምግብና የመዝናኛ አገልግሎቶች የሚታወቀው ስፍራ፣ ለመንገዱ መስፋፋትና ለከተማዋ አዲስ የውበት ግንባታ ሲባል እንዲነሳ ተደረጓል። ከፉድ ዞን በተጨማሪም በመስመሩ ላይ የነበሩ በርካታ አነስተኛ ሱቆችና ሰፋፊ ቦታዎችን ይዘው የነበሩ የመኪና መሸጫዎች (Car Sales) መፍረሳቸውን ፊደል ፖስት መታዘብ ችሏል።

​ይህ የፈረሳና የግንባታ ሂደት በአካባቢው የትራፊክ ፍሰት ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ይገኛል። ቦሌ መድኃኒዓለም እና አትላስን የሚያገናኘው ይህ ቁልፍ መንገድ የከተማዋ የንግድና የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ማዕከል በመሆኑ፣ የመንገዱ መጥበብና የግንባታ ቁሳቁሶች ክምችት ለተሽከርካሪዎች መጨናነቅ ምክንያት ሆኗል።

አሽከርካሪዎችና ነዋሪዎች የዕለት ተዕለት ውሏቸው ላይ መስተጓጎል ቢገጥማቸውም፣ ግንባታው በፈጣን ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን መመልከት ችለናል።

​ምንም እንኳን እንደ ፉድ ዞን ያሉ የንግድ ስፍራዎች መፍረስ ለደንበኞቻቸውና ለባለቤቶቹ ድንገተኛ ቢሆንም፣ የኮሪደር ልማቱ ሲጠናቀቅ የአካባቢውን ገጽታ ለውጦ ምቹ የእግር መንገድና ዘመናዊ መሠረተ ልማት እንደሚዘረጋ ይጠበቃል። መንግስት ይህን ፕሮጀክት ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ሳቢና ለዓለም አቀፍ ደረጃ የምትመች ለማድረግ እያከናወነው ያለ ትልቅ ስራ እንደሆነ ይገልጻል።

የግንባታው መጠናቀቅ አሁን ያለውን የትራፊክ መጨናነቅ በመቅረፍ ረገድም ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ይታመናል።
9 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.