Logo
YenetaTube
ኢትዮጵያ ከ10 ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ከኒውክሌር ቴክኖሎጂ ኃይል ማመንጨት ትጀምራለች

ኢትዮጵያ ከ10 ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የኒውክሌር ቴክኖሎጂን በመገንባት የኃይል ማመንጨት እንደምትጀምር የኢትዮጵያ የኒውክሌር ኢነርጂ ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አብዱረዛቅ ዑመር ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የኒውክሌር ቴክኖሎጂን ለመገንባት ከ10 እስከ 15 ዓመታት የሚፈጅ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ አሁን ባለው የቅድመ ዝግጅት ፍጥነት ከ10 ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ ለመግባት አቅዳ እየሠራች ነው።

ለዚህም የኒውክሌር ልማት ሥራውን በኃላፊነት መወጣት የሚችል ተቋም ተቋቁሞ አስፈላጊ መሠረተ ልማቶችን የመገንባትና ከጥንቃቄና ደኅንነት አኳያ የሚከናወኑ ተግባራት እየተሠሩ መሆኑን አብዱረዛቅ ዑመር አስረድተዋል።

የኒውክሌር ልማት ፕሮግራሙ የኃይል አቅርቦትን ከአየር ንብረት ጋር በተጣጣመ መልኩ አስተማማኝ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ምክትል ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል።

ቴክኖሎጂው በጤና፣ በኢንዱስትሪና በግብርና ዘርፎች ምርታማነትን ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸው፤ ኒውክሌር ኃይልን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለልማት ለማዋል ግንዛቤ መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር መጀመሩን ተናግረዋል።

ይህ አስተማማኝ የኃይል ምንጭ ሀገሪቱ ለምታደርገው ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ተመላክቷል።

Via ጋዜጣ ፕላስ

9 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.