Logo
Getu Temesgen
የ“አእላፋት ዝማሬ” በአዲስ አበባ በመስቀል አደባባይና በድሬዳዋ ከተማ ይካሄዳል
#ethiopia | ለሦስተኛ ጊዜ የሚካሄደውና “በመንፈስ ቅዱስ የተሰናዳ የሰላም መዝሙር” ተብሎ በቅዱስ ፓትርያርኩ የተገለጸው የ“አእላፋት ዝማሬ” መርሐ ግብር፤ የፊታችን ማክሰኞ ታኅሣሥ 28 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይና በድሬዳዋ ለገሃር አደባባይ በድምቀት እንደሚከናወን የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ትውልድ ማኅበር (ኢጃት) አስታወቀ።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በቦሌ መድኃኔዓለም ካቴድራል ሲካሄድ የቆየው ይህ ዝማሬ፤ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰፋ ባለ ቦታ በመስቀል አደባባይ እንዲካሄድ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነትና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሙሉ የድጋፍ ደብዳቤና ሕጋዊ ፈቃድ ማግኘቱን ማኅበሩ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ገልጿል። ይህም ቦታ የተመረጠው ባለፉት ዓመታት በነበረው ከፍተኛ የምእመናን ቁጥር ምክንያት የተፈጠረውን መጨናነቅ ለመቀነስና የምእመናንን ደኅንነት ለመጠበቅ ታስቦ መሆኑ ኢጃት በሰጠው መግለጫ አሳውቋል።

በዘንድሮው ዝግጅት 30 የሚሆኑ መዝሙራት በኅብረት የሚዘመሩ ሲሆን፣ ዝግጅቱ ከቀኑ 9:00 ሰዓት ጀምሮ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩና በብፁዓን አባቶች ጸሎትና ቡራኬ ተከፍቶ እስከ ምሽቱ 1:30 ድረስ ይቆያል። መርሐ ግብሩ በጊዜ እንዲጠናቀቅ የተደረገውም ምእመናን ወደየአጥቢያቸው ተመልሰው በበዓሉ ዋዜማ የሚከናወነውን ማኅሌትና ቅዳሴ እንዲሳተፉ ለማስቻል እንደሆነ ተገልጿል።

ምእመናን በዕለቱ የቅዱሳን መላእክትና የሰማዕታት ምሳሌ የሆነውን ነጭ ልብስ ለብሰው እንዲገኙ ጥሪ የቀረበ ሲሆን፣ ለታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም የሚሰጥ የጧፍ መባዕ ይዘው እንዲመጡም ተጠይቋል። በተጨማሪም አረጋውያንና አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረገ ልዩ የመቀመጫ ቦታ፣ የሕክምና አገልግሎትና የትራንስፖርት አማራጮች መዘጋጀታቸው በመግለጫው ተመልክቷል።

በዕለቱ የጸጥታ ፍተሻን በትዕግሥት በማለፍ ኦርቶዶክሳዊ ጨዋነትን በተሞላበት መንገድ መርሐ ግብሩን እንዲታደሙ ያሳሰበው ማኅበሩ፤ ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትን ይዞ አለመምጣትና ካሜራ ይዞ አለመግባት ለሥርዓቱ መከበር አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝቧል። በአካል መገኘት ለማይችሉ ምእመናን ደግሞ በጃንደረባው ሚዲያና በተለያዩ የሀገር ውስጥ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ቀጥታ ሥርጭት እንደሚተላለፍ ታውቋል።

ለዚህ ታላቅ መንፈሳዊ ጉዞ ስኬት አስተዋጽኦ ላደረጉት የቤተ ክህነት አባቶች፣ የመንግሥት አካላትና ደጋፊዎች ማኅበሩ ምስጋናውን አቅርቧል።

Getu Temesgen - (ጌጡ ተመስገን)

9 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.