Logo
FIDEL POST NEWS
የጉራጊኛ ቋንቋን በስርዓተ ትምህርት ዉስጥ እስከ 8ኛ ክፍል ለማካተት እየተሰራ ነዉ ተባለ

የጉራጊኛ ቋንቋን ለማሳደግ በትምህርት ስርዓቱ ዉስጥ የማካተት ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉ የተገለፀ ሲሆን በ2017 የትምህርት ዘመን በሙከራ ደረጃ የነበረዉ የ2ኛ ክፍል የጉራጊኛ ትምህርት ወደ ሙሉ ትግበራ መግባቱን የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ አስታዉቋል ።

በዞኑ ጉራጊኛ ቋንቋ በ2017 ዓ.ም የስራ ፣የሚዲያና የትምህርት ቋንቋ እንዲሆን በምክር ቤት መወሰኑን ተከትሎ ቋንቋዉን ይበልጥ ለማሳደግ በቋንቋዉ ከማዉራት ባለፈ በስርዓተ ትምህርት ዉስጥ የማካተት ሂደት በዘንድሮ አመት በ3ኛ ክፍል በ18 ትምህርት ቤቶች በሙከራ ደረጃ እንደሚሰጥ የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መብራቴ ወልደማሪያም ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል ።

በዞኑ ባለፉት ዓመታት የጉራጊኛ ትምህርት በቅድመ መጀበኛና በአንደኛ ክፍል በሙሉ ትግበራ መሰጠቱን ለጣቢያችን የተናገሩት ኃላፊዉ አምና በሙከራ ደረጃ የነበረዉ የ2ኛ ክፍል የጉራጊኛ ትምህርት በሙሉ ትግበራ መሰጠት መጀመሩን ገልፀዋል ።ለዚህም በዞኑ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ከ13ሺህ 5 መቶ የመማሪያና ማስተማሪያ መፅሀፍት ማሳተም መቻሉ ተናግሯል ።

በቀጣይ ዓመት የ3ኛ ክፍል የጉራጊኛ ትምህርት በሁሉም ትምህርት ቤቶች ወደ ትግበራ እንደሚገባ ተገልጿል ።በተጨማሪም በቀጣይ አራት እና አምስት ዓመታት ዉስጥ የጉራጊኛ ትምህርትን በስርዓተ ትምህርቱ ዉስጥ እስከ 8ኛ ክፍል ለማካተት እየተሰራ መሆኑን የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መብራቴ ወልደማሪያም ከጣቢያችን ጋር በነበራቸዉ ቆይታ ገልጸዋል ።

በመባ ወርቅነህ
#ዳጉ_ጆርናል
10 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.