Logo
Getu Temesgen
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ፡

📌ግብፅ ቅኝ ገዥያዊ አስተሳሰቧን አሽቀንጥራ በመጣል ወደ ትብብርና ውይይት እንድትመጣ አሳሰበ
#ethiopia | የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከቅኝ ግዛት ዘመን ባልተላቀቀ አስተሳሰብ ተይዘዋል ያላቸው የግብፅ ባለሥልጣናት የሚያሰሟቸውን ተደጋጋሚ የውይይት ክልከላና በግልጽም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚሰነዘሩ ማስፈራሪያዎችን አጥብቆ ኮነነ። ሚኒስቴሩ ይህን ያስታወቀው ለሕዝብ ይፋ ባደረገው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።

የግብፅ ባለሥልጣናት የሚያሰሟቸው ተደጋጋሚ ውይይትን በአጽንዖት የሚሽሩ መግለጫዎች፣ እንዲሁም በግልጽም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚሰነዘሩ ማስፈራሪያዎች የግብፅ መንግሥት የ21ኛውን ክፍለ ዘመን እውነታዎች መቀበል አለመቻሉን የሚያሳዩ መገለጫዎች መሆናቸውን መግለጫው አመላክቷል።

"በቅኝ ግዛት ዘመን አስተሳሰብ የተጠመቁ አንዳንድ የግብፅ ባለሥልጣናት በናይል ወንዝ ውኃ ላይ ብቸኛ ባለቤትነት እንዳላቸው ያስባሉ። የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነቶችን በመጥቀስ 'በታሪክ የተረጋገጠ መብት' የሚሏቸውን አቋማቸውን ያሰማሉ።"
ካይሮ የፈለገችውን የሚያደርጉ ደካማና የተከፋፈሉ ጥገኛ መንግሥታት እንዲኖሯት በማሰብ የግብፅ ባለሥልጣናት በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ኢትዮጵያን ያካተተ ግን በእሷ ብቻ ያልተገደበ የማተራመስ ዘመቻ እያካሄዱ እንደሆነ ሚኒስቴሩ ገልጿል። ይህ “የተሳሳተ አካሄድና ጥረት የአመራርና የአስተሳሰብ ድክመት” ውጤት መሆኑን አስረድቷል።

ኢትዮጵያ ይህን “ኢትዮጵያን በፍፁም ያላንበረከከው ጊዜ ያለፈበት የጥቃት አካሄድ” ለመተው ጊዜው አሁን መሆኑን ጠቁማለች።

ኢትዮጵያ በፓን አፍሪካኒዝም ላይ ያላት ጽኑ አቋም እና በአህጉሪቱ በነበሩ የፀረ-ቅኝ ግዛት ትግሎች ሁሉ ድጋፍ ያደረገችበት ረዥም እና ኩሩ ታሪክ እንዳላት ገልጿል። በመሆኑም፡

"ኢትዮጵያ ካይሮ ለማስወገድ እየተቸገረች ያለችውን የቅኝ አገዛዝ ቅርሶችን የምታስተናግድበት ቦታ የላትም
።
"ከአገር ውስጥ የሚመነጨው አባይ ወንዝ ለናይል ተፋሰስ ውኃ 86% ያህል አስተዋፅዖ የሚያደርግ ሲሆን፣ የአባይ ተፋሰስ የኢትዮጵያን 70% የገፀ ምድር ውኃ ይሸፍናል

።
።
"ኢትዮጵያ ልክ እንደሌሎቹ ተፋሰስ አገራት ሁሉ ይህን የተፈጥሮ ሃብት የመጠቀም መብት አላት። ፍትሐዊ፣ ምክንያታዊ እና ፍትሃዊ አጠቃቀም በዚህ ሁኔታ ተፈፃሚነት ያለው ዓለም አቀፍ ሕግ መሠረታዊ መርህ ነ
ው
።
" ኢትዮጵያ በወሰኗ ውስጥ የሚገኘውን የተፈጥሮ ሃብት ለመጠቀም ከማንም ፈቃድ የመጠየቅ ግዴታ እንደሌለባት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫው በድጋሚ አጽንቷል።

በቀድሞ ጊዜ ግብፅ ለድርድር የቀረበች በማስመሰል በእንቅፋትና ብቸኛ የውኃ ባለቤትነት ጥያቄዋ መፍትሔ እንዳይመጣ ስታደርግ ቆይታለች። አሁን ግን ውይይትን የመካድ እና የጠላትነት ንግግሯን የማጠናከር ፖሊሲ ይፋዊ ሆኗል። ግብፅ ውይይትን በመካድ ግጭትን ለመቀስቀስ እየሞከረች ነው።

ሚኒስቴሩ ይህንን “ኃላፊነት የጎደለው ባህሪ” ያሳሰባቸው አካላት ሁሉ እንዲያወግዙት ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ የልማት ምኞቶች እና እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያሉ ፕሮጀክቶች “የአፍሪካ የራስ መተማመን እና እድገት መገለጫዎች” ናቸው።

ካይሮ በምትሰራው አሉባልታና ንግግር ከመጠመድ ይልቅ ከኢትዮጵያ ልማት ጋር አብሮ ለመኖር መማር እና ለጋራ ብልጽግናና ልማት በቅን ልቦና ወደ ትብብር ማዕቀፍ ለመሥራት መወሰን ብልህ አካሄድ መሆኑን መግለጫው አመላክቷል።

ዓለም እና አፍሪካ የሚፈልጉት ግጭትና መናቆር ሳይሆን የበለጠ ትብብርና ውይይት ነው።

ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝን አሁን ያለውንና ወደፊት የሚመጣውን ትውልድ ፍላጎት ለማሟላት የመጠቀም መብቷን በማረጋገጥ ጽኑ አቋም እንዳላትና በፍትህና በእኩልነት መርሆዎች ላይ የተመሠረተ ለሁለቱም ወገኖች የሚጠቅም መፍትሔ ለመፈለግ ክፍት መሆኗን ገልጻለች። #menaharia_fm

10 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.