Logo
Getu Temesgen
አፍሪካን የመገንባት ራዕይ
#ethiopia | እሳቸው አንድ ሰው ቢሆኑም ራዕያቸው ግን መላው አፍሪካን እያዳረሳት ይገኛል፡፡

በመላው ናይጄሪያ ውስጥ በየቀኑ ከሚመገቡት ጨው አንስቶ እስከሚራመዱበት መንገድ ድረስ ዘልቆ በመግባት የእያንዳንዱን ሰው ሕይወት ይዳስሳሉ።

አያታቸው በእሳቸው አስተዳደግ ውስጥ ከፍተኛ ሚና እንደተጫወቱ ይነገራል፡፡

በልጅ ልጃቸው ውስጥ ያለውን የስራ ፈጣሪነት መንፈስ ለማነሳሳትም ረድተዋል፡፡

የስምንት ዓመት ልጅ እያሉ ከአያታቸው የተሰጣቸውን የኪስ ገንዘብ ጣፋጭ ነገር በመግዛት ለሌሎች አትርፈው ይሸጡም ነበር፡፡

በግብፅ ካይሮ ከሚገኘው የአል-አዛሃር ዩኒቨርሲቲ የተመረቁት ዳንጎቴ፤ የቢዝነስ ስራቸውን የጀመሩት እንደ ትልቅ ተቋም ሳይሆን መጠነኛ የንግድ ድርጅት በመጀመር ነው።

ከሸቀጥ ንግድ እስከ ዓለም አቀፍ ግዙፍ ኢንዱስትሪ ጅማሬው ከዚህ ተነስቷል፡፡

የዳንጎቴ መስራች አሊኮ ዳንጎቴ በሲሚንቶ፣ በስኳርና በዱቄት በመሳሰሉት ሸቀጦች በመገበያየት፣ በማስመጣትና ናይጄሪያ ውስጥ በመሸጥ ነበር የስኬት ጉዞአቸውን የጀመሩት።

ጅማሬያቸው ቀላል መስሎ ቢታይም መዳረሻቸው ልቆና ገዝፎ ተገኘ፡፡

ገና በለጋነታቸው ‹‹ችግር የሥኬት ምንጭ ነው›› የሚለውን የቢዚነስ እሳቤ የተረዱ ይመስላል፡፡

በዚህ እሳቤ ሰዎች በየቀኑ የሚፈልጓቸውን ሸቀጦች መለየትና አቅርቦታቸውን መቆጣጠርም ጀመሩ።

ፍልስፍናቸው አንድ ሀገር ከሌሎች ሀገራት የሚያስመጣውን ምርት በሀገር ውስጥ ማምረት እንዳለበት ያወሳል።

ይህ ስልትም ዳንጎቴ ነጋዴ ብቻ ሳይሆኑ ብሄራዊ ስትራቴጂስትም አድርጓቸዋል።

በተግባርም ናይጄሪያን ከሲሚንቶ አስመጪነት ወደ ላኪነት ቀይሯታል፡፡

በምዕራብ አፍሪካ ውስጥ የትኛውንም ትልቅ ግንባታ ካዩ መሰረቱ በዳንጎቴ ሲሚንቶ የጸና ነው።

ዳንጎቴ እ.ኤ.አ በ1990ዎቹ መገባደጃ ላይ ከስኳር ማጣሪያ ጀምሮ የራሳቸውን የምርት ፋብሪካዎች መገንባት ጀመሩ።

ይህ ርምጃ ንግድን ከከባቢው ጋር በማዋሀድ ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካትም አስቻለ፡፡

ከትሁት ጅማሬዎች እስከ አህጉራዊ የበላይነትንም እንዲቀዳጁ አስቻላቸው፡፡

በዚህም በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በሲሚንቶ ማምረት፣ ነዳጅ በመፈለግ፣ ማዕድን በማውጣት፤ የማዳበሪያ ፋብሪካ በመገንባት፣ የተፈጥሮ ጋዝ በማጓጓዣ እና በሌሎች ዘርፎች ላይ ተሰማርተዋል፡፡

የዳንጎቴ ትጋት የጀመረው ከተደላደለ ሁኔታ ሳይሆን በድፍረት፣ በብድር እና በማያቋርጥ ራዕይ ነው።

ወጣት በነበሩበት ጊዜ ከአጎታቸው አነስተኛ ገንዘብ ተበድረው የዛሬ መዳረሻቸውን አንድ ርምጃ ተራመዱ፡፡

በሌጎስ፣ ናይጄሪያ በአንደ የንግድ ቦታ የተጀመረው ስራ ጉዞውን ቀጠለ፡፡

ዳንጎቴ ትክክለኛው ሀብት በማኑፋክቸሪንግ ውስጥ እንዳለ በመገንዘብ በፍጥነት ከመሸጥ ወደ ማምረት ገቡ።

በመጀመሪያም በስኳር ማጣሪያ፣ ከዚያም በጨው ፋብሪካ እና ሲሚንቶ እያሉ ዛሬም ያልታጎለው ጉዞአቸውን ቀጥሏል፡፡

ዛሬ የዳንጎቴ ኢንደስትሪ የባለብዙ ቢሊየን ዶላሮች ባለቤት ሲሆን፤ የአህጉሪቱ ትልቁ ሲሚንቶ አምራች ሆኗል፡፡

ይህም በናይጄሪያና በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የሚሰራ ነው።

እንዲሁም የዳንጎቴ ስኳር ማጣሪያ የገበያ መሪ ሲሆን፤ የጨው ምርቱም በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ቶን ያመርታል።

በዘይት እና ጋዝም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በስፋት እየሰሩበት ይገኛል፡፡

አፍሪካ ሰፊ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ያላት አህጉር ብትሆንም ለበርካታ አስርት ዓመታት ያክል ከሌሎች ስትገለገል ቆይታለች።

ታዲያ ዳንጎቴ ይህንን ችግር ልብ ያሉ ይመስላል። ለዚህም ኩባንያቸው በሌጎስ ናይጄሪያ የሚገኘውን የዳንጎቴ ማዳበሪያ ፋብሪካ ፕሮጀክት አስጀመረ።

ይህ ፋብሪካም በዓለም ላይ ትልቁ የዩሪያ ማዳበሪያ ማምረቻ ሲሆን፤ በዓመት 3 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የማምረት አቅም አለው፡፡

ናይጄሪያ በማዳበሪያ ራሷን እንድትችል እና ለዓለም አቀፍ ገበያ በተለይም ለአፍሪካና ለአሜሪካ ከፍተኛ ኤክስፖርት ማድረግ እንድትችል የተጀመረ ውጥን ነው፡፡

ይህ ተቋም በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ አርሶ አደሮች የሰብል ምርትን የማሳደግ፣ የግብርና ኢኮኖሚን ​​የማረጋጋትና የዓለም የማዳበሪያ ንግድ ቀመርን የመቀየር ኃይልን ተቀዳጅቷል።

ይህም አፍሪካ እራሷን መመገብ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፋዊ የግብርና ንግድ ውስጥ ወሳኝ ተዋናይ መሆን እንደምትችል አመላካች ሆኗል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህም አድማሱን እያሰፋ የመጣው የዳንጎቴ ቡድን የኢትዮጵያን ኢንዱስትሪ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ሊያቀና ተሰልፏል።

ለዚህም በ2007 ዓ.ም ያስመረቀው ግዙፍ የሲሚንቶ ፋብሪካ ተጠቃሽ ነው።

የዳንጎቴ ወደ ኢትዮጵያ መግባት የቅርብ ጊዜ ጅማሮ ሳይሆን የረጅም ጊዜ ስትራቴጂካዊ ውጥን ነው።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ፈጣን ኢኮኖሚ እያስመዘገቡ ካሉና ለኢንዱስትሪ መስፋፋት ከፍተኛ ፍላጎት ያላት መሆኑን በመገንዘብ ድርጅታቸው ከዓመታት በፊት በሲሚንቶ ማምረት ወደሀገሪቱ ገብቷል፡፡

ይህ ርምጃ የኢትዮጵያን ሥር የሰደደ የሲሚንቶ እጥረት ለማስቆም እና ግዙፍ የግንባታ ግስጋሴዋን የሚደግፍ እና የዳንጎቴን ቡድን ታዋቂነትን ወደ ወሳኝ ምዕራፍ በማሸጋገር ላይም ይገኛል።

ስምምነቱ የዳንጎቴ ቡድን በሙያው ባለባቸው ዘርፎች ላይ ኢንቨስት እንዲያደርግ መንገድ የሚከፍት ሲሆን፤ ከነዚህም መካከል በማዳበሪያ ምርት የናይጄሪያውን ስኬት በመጠቀም በኢትዮጵያ የማዳበሪያ ማምረቻ ፋብሪካ ለመገንባት ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ ይገኛል።

ይህም የኢትዮጵያ መንግሥት በምግብ ራስን የመቻል ራዕይ ጋር በቀጥታ የሚጣጣም ነው።

በዚህም ኢትዮጵያ ሲሚንቶና ማዳበሪያን በሀገር ውስጥ በማምረት ለገቢ ንግድ የምታወጣውን በቢሊዮን የሚቆጠር የውጭ ምንዛሪ ማዳን እንድትችል የሚያግዝ ነው።

ይህ ተግባርም በሺዎች ለሚቆጠሩ ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆኑ የስራ እድል በመፍጠር የሀገር ውስጥ ኢኮኖሚን ​​ያሳድጋል።

እንዲሁም የዳንጎቴ ቡድን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የማኑፋክቸሪንግ እውቀትና ቴክኖሎጂን በማምጣት የኢትዮጵያን አጠቃላይ የኢንዱስትሪ ስነ-ምህዳር ከፍ ያደርገዋል።

ኢትዮጵያ የራሷን ሲሚንቶ፣ ማዳበሪያና ሌሎችም ምርቶች ወደ ሰፊው የምስራቅ አፍሪካ ገበያ ኤክስፖርት ማድረግ እንድትችልም ያደርጋታል፡፡

የዳንጎቴ ግሩፕ በአፍሪካ ውስጥ የሚሰራ ኩባንያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ የኢንዱስትሪ እጣ ፈንታ ቀያሽ መሐንዲስም እየሆነ ነው።

ከናይጄሪያ በተጨማሪ በኢትዮጵያ፣ ታንዛኒያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ዛምቢያ፣ ሴኔጋል፣ ካሜሮን፣ ኮንጎ፣ ጋና፣ ሴራሊዮንና ኮትዲቭዋር የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን ገንብተዋል።

በናይጄሪያ ሌጎስ የአፍሪካ ግዙፉን የነዳጅ ማጣሪያ በመገንባትም ጋና እና ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ ለአፍሪካ ሀገራት ነዳጅ ያቀርባል።

በአሁኑ ወቅት ከ17 በላይ በሆኑ የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ ተሳትፎ ያለው ሲሆን፤ በአህጉሪቱ የሲሚንቶ ገበያም መሪ ነው።

ዳንጎቴ የንግድ ድርጅት ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ የአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ እጣ ፈንታ እየቀረጸ ይገኛል።

ሀገራት ለግንባታ የሚውል ሲሚንቶ፣ ለምግብ ማዳበሪያ እና ለኃይል ማመንጫ የተጣራ ነዳጅ በሀገር ውስጥ ማምረት እንዲችሉም ድጋፍ በማድረግ ላይ ነው።

በቅርቡ ከኢትዮጵያ ጋር የተደረሰው ታሪካዊ ስምምነትም አፍሪካ እራሷን እንድትችል እና ኢኮኖሚያዊ ብልጽግናን ለማምጣት ያለውን ተልእኮ የሚያሳይ ነው ሲል ጋዜጣ+ ዘግቧል።

12 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.